የኢሬቻን ሀገራዊ እሴቶች ጥንካሬ በትውልዱ ውስጥ በማስረጽ እያጠናከሩ መሄድ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ይጠበቃል - ኢዜአ አማርኛ
የኢሬቻን ሀገራዊ እሴቶች ጥንካሬ በትውልዱ ውስጥ በማስረጽ እያጠናከሩ መሄድ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ይጠበቃል

አዲስ አበባ፤ መስከረም 20/2018(ኢዜአ)፦ የኢሬቻን ሀገራዊ እሴቶች ጥንካሬ በትውልዱ ውስጥ በማስረጽ እያጠናከሩ መሄድ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት እንደሚጠበቅ የኦሮሚያ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ሃላፊ ሃይሉ አዱኛ ተናገሩ።
"ኢሬቻ ለሀገር ማንሰራራት" በሚል መሪ ሀሳብ የሚከበረውን የዘንድሮው ኢሬቻ በዓል ላይ ያተኮረ 'ጉሚ በለል' የውይይት መድረክ በክልሉ ፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት እና በኮሙኒኬሽን ቢሮ ትብብር ተካሂዷል።
በውይይት መድረኩ ላይ የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ቢሮው ኃላፊ ሃይሉ አዱኛ፤ የገዳ ስርዓት ትሩፋት የሆነውን የኢሬቻ በዓል የበለጠ ለማጠናከር ከባለድርሻ አካላት ብዙ ይጠበቃል ብለዋል።
ኢሬቻ ከሰላም፣ እርቅ እና አንድነት ጀምሮ በሀገር ግንባታ እና ህብረ ብሔራዊ እንድነትን ከማጠናከር አንጻር በርካታ ሀገራዊ እሴቶች ያሉት መሆኑን ተናግረዋል።
እነዚህን እሴቶች በጎ አስተዋጽኦ የበለጠ በማጠናከር ለትውልድ ግንባታ ማዋል እንደሚገባ አመልክተው ለዚህም ሁሉም ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።
የኢሬቻ በዓል ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣ በዓል መሆኑን አንስተው፤ የዘንድሮው ኢሬቻ በተሻለ መልኩ እሴቱን በጠበቀ መልኩ እንዲከበር ዝግጅት ተደርጓል ነው ያሉት።
በመድረኩ ላይ የውይይት መነሻ ጽሁፍ ያቀረቡት በአርሲ ዩኒቨርሲቲ የገዳ ትምህርት መምህር መሐመድ ነሞ(ዶ/ር)፣ ኢሬቻ የበለጠ እንዲያድግ በቅንጅት መስራት እንደሚገባ አመልክተዋል።
በዓሉን ከሀገር ውስጥ አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ በማስተዋወቅ በቱሪዝም ዘርፉ ትልቅ የገቢ ምንጭ ማድረግ እንዲቻል የባለድርሻ አካላት ሚናም ማደግ እንዳለበት አስረድተዋል።
በባህልና ቋንቋ ዘርፍ የተሰማሩ ባለሙያዎችም የበዓሉን በጎ ገጽታ ማጉላት የሚያስችሉ የጥናትና ምርምር ስራዎችን ማጠናከር እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
አስተያየታቸውን የሰጡ የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው የገዳ ስርዓት አንዱ አካል የሆነው ኢሬቻ የኦሮሞ ህዝብ ለፈጣሪው ምስጋና የሚያቀርብበት እንዲሁም ህብረትና ትስስር የሚያጠናክርበት ነው ብለዋል።
በአጠቃላይ የኢሬቻ በዓል አብሮነት፣ ይቅርታ፣ እርቅ፣ አንድነትና መተባባር የሚጎለብትበት መሆኑን ጠቅሰው የተጀመረውን የሀገረ መንግስት ግንባታ እውን ለማድረግ የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል።
የዘንድሮው ኢሬቻ እሴቱን በጠበቀ መልኩ እንዲከበር የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውንም ገልጸዋል።