ቀጥታ፡

በጋሞ ዞን በ25 ሺህ ሄክታር መሬት ተፋሰስ ላይ የተቀናጀ የውሃ ሃብት አስተዳደር ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

አርባ ምንጭ፤ መስከረም 20/2018 (ኢዜአ):- በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጋሞ ዞን በ25 ሺህ ሄክታር መሬት ተፋሰስ ላይ የተቀናጀ የውሃ ሃብት አስተዳደር ፕሮጀክት ይፋ ሆነ።

በዞኑ በሚገኘው "የሃሬ ተፋሰስ" የተቀናጀ የውሃ አስተዳደር ፕሮጀክት አተገባበር ዙሪያ የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ በአርባ ምንጭ ከተማ ተካሄዷል።

በመድረኩ ላይ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ውሃ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዳንኤል ዳሌ (ዶ/ር)፤ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ፕሮጀክቱ የስምጥ ሸለቆ ሀይቅ የሆነውን የአባያን ሀይቅ ማዕከል አድርጎ የሚተገበር መሆኑን ተናግረዋል።


 

በዞኑ በ25 ሺህ ሄክታር መሬት ተፋሰስ ላይ የተቀናጀ የውሃ ሃብት አስተዳደር ፕሮጀክት ይፋ መደረጉን ገልጸዋል።

ፕሮጀክቱ የውሃ ጥራትን በማስጠበቅ፣ የተጎዳ መሬት መልሶ እንዲያገግም በማድረግ እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚችል አካባቢን ለመፍጠር የላቀ ፋይዳ ያለው መሆኑን አስረድተዋል።

የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ማማሩ አያሌው (ዶ/ር)፤ የፕሮጀክቱ  ዓላማ የተፋሰሱ ነዋሪዎችን ኑሮ ማሻሻል እና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አካባቢ ለመፍጠር መሆኑን ተናግረዋል።


 

በፕሮጀክቱ ንጹህ ውሃን ተደራሽ ማድረግ፣ የአፈር ክለት መጠንን መቀነስ፣ ለመጠጥና ለመስኖ መሠረተ ልማት ዝርጋታ ምቹ ሁኔታን መፍጠር እንዲሁም የህብረተሰቡን የግንዛቤ መጠን ማሳደግ ተግባራት ትኩረት መሰጠቱን አስረድተዋል።

በአባያ ሃይቅ ላይ ችግር እየፈጠረ ያለውን ደለል ለመቀነስ የሚደረገውን ጥረት በማገዝ ረገድም የጎላ ሚና አለው ብለዋል።

የጋሞ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ማገሶ ማሾሌ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ በጋሞ ዞን ዲታ፣ ጨንቻ ዙሪያ፣ አርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳዎችንና አርባ ምንጭ ከተማን ጨምሮ የ32 ቀበሌዎች ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ያደርጋል ብለዋል።


 

የተቀናጀ የውሃ ሃብት አስተዳደር ፕሮጀክት ለመሬት አስተዳደር ስርዓትም ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ጠቁመው ለተግባሩ መሳካት አጋዥ ሊሆኑ የሚችሉ ችግኞችን ለማቅረብ በቂ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።

የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር ፕሮጀክት በሀገራችን በስምጥ ሸለቆ ሀይቆች በተለይ በአባያ፣ በአዋሽ፣ በኦሞ ጊቤ እና በተከዜ ተፋሰሶች ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራም ተመልክቷል።

የ''ሃሬ ተፋሰስ'' የተቀናጀ የውሃ ሃብት አስተዳደር የ5 ዓመት ፕሮጀክት ሲሆን ለተግባራዊነቱም በ21 ተቋማት መካከል የድርጊት መርሃ ግብር ስምምነት ተደርጓል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም