ቀጥታ፡

ብዝኃ ሕይወት የህልውና መሰረትና የኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት በመሆኑ በሁሉም የልማት ዕቅዶች መካተት አለበት

አዲስ አበባ፤ መስከረም 20/2018(ኢዜአ)፦ ብዝኃ ሕይወት የህልውና መሰረትና የኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት በመሆኑ በሁሉም የልማት ዕቅዶች መካተት እንዳለበት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሰለሞን ላሌ ገለጹ፡፡

ብሔራዊ የብዝኃ ሕይወት ዓመታዊ ጉባኤ በቢሾፍቱ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡

በመርሃ ግብሩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሰለሞን ላሌ፣ የኢትዮጵያ ብዝኃ ሕይወት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ካርታ ካስኬ(ዶ/ር)፣ የፌደራልና የክልሎች የሥራ ኃላፊዎችና የዘርፉ ባለሙያዎች ተገኝተዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ሰለሞን ላሌ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ዓለም አቀፍ የብዝኃ ሕይወት ስምምነት ዓላማው ብዝኃ ሕይወትን በማንበር ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ማስፈን ነው፡፡

በኢትዮጵያ እ.አ.አ ከ2025 እስከ 2030 ድረስ የሚተገበረው ብሔራዊ የብዝኃ ሕይወት ስትራቴጂና የድርጊት መርሃ ግብር ጸድቆ ወደ ስራ መግባቱን ተናግረዋል፡፡

ብሔራዊ የብዝኃ ሕይወት ስትራቴጂና የድርጊት መርሃ ግብሩ በኢትዮጵያ ሥራ ላይ የዋሉ ፖሊሲዎችን፣ ልምዶችና የሀገሪቱን የፋይናንስ አቅም ታሳቢ በማድረግ ዓለም አቀፍ ደረጃውን ጠብቆ መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡

ብዝኃ ሕይወት የህልውናችን መሰረትና የኢኮኖሚያችን የጀርባ አጥንት ነው ያሉት የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢው፤ ስትራቴጂውና የድርጊት መርሃ ግብሩን በአግባቡ ተርጉሞ ገቢራዊ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ለዚህ ደግሞ ብዝኃ ሕይወትን በሁሉም የልማት እቅዶች በማካተት ለስትራቴጂውና ለድርጊት መርሃ ግብሩ ስኬት በጋራ መረባረብ ይገባል ብለዋል፡፡

ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት የጎላ አበርክቶ እንዳለው በመጥቀስ፤ ተግባራዊነቱን በክትትልና ቁጥጥር ሥራዎች ማረጋገጥ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብዝኃ ሕይወት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ካርታ ካስኬ(ዶ/ር)፤ የብዝኃ ሕይወት ስትራቴጂና የድርጊት መርሃ ግብር 18 በሚደርሱ ተቋማት የተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ስትራቴጂውና የድርጊት መርሃ ግብሩ ጸድቆ ወደ ስራ መግባቱ ፋይዳው የጎላ መሆኑን በማንሳት፤ ለሀገራችን የተፈጥሮ ሀብትና ብዝኃ ሕይወት ጥበቃ ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡

የብዝኃ ሕይወት ስትራቴጂና የድርጊት መርሃ ግብሩ ከኢትዮጵያ የ10 ዓመት መሪ የልማት ዕቅድ የተጣጣመ መሆኑን በመጥቀስ፤ ሁለንተናዊ ዕድገትን ማረጋገጥ እንደሚያስችል ገልጸዋል፡፡

የግብርናና ዘርፉ ተዋንያን ለብሔራዊ ብዝኃ ሕይወት ስትራቴጂና የድርጊት መርሃ ግብር ትግበራ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማበረከት አለባቸውም ነው ያሉት፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም