ቀጥታ፡

በድሬደዋ ጤናማና አምራች ማህበረሰብ ለመፍጠር የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው ቀጥለዋል- ከንቲባ ከድር ጁሃር

ድሬደዋ፤ መስከረም 20/2018(ኢዜአ)፦ በድሬደዋ የጤናን ጥራትና ፍትሃዊ ተደራሽነት በማስፋት አምራች ማህበረሰብ ለመፍጠር የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠላቸውን የአስተዳደሩ ከንቲባ ከድር ጁሃር ተናገሩ።



 

የሳብያን ጠቅላላ ሆስፒታል ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ ያስገነባው ዘመናዊ የፅኑ ህሙማን ህክምና ማዕከል ከንቲባ ከድር ጁሃር፣ የአስተዳደሩ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ፅጌረዳ ክፍሌና የሆስፒታሉ አመራሮች በተገኙበት ዛሬ ተመርቋል።

ከንቲባ ከድር በወቅቱ እንደገለፁት፤ በአስተዳደሩ በከተማና ገጠር ወረዳዎች የጤናን ፍትሃዊ ተደራሽነትና ጥራት በማረጋገጥ  ጤናማና አምራች ማህበረሰብ ለመፍጠር ስራዎች እየተከናወኑ ናቸው።


 

ዛሬ በሳቢያን ጠቅላላ ሆስፒታል ወደ አገልግሎት የተሸጋገረው የፅኑ ህሙማን ህክምና ማዕከል የዚህ ጥረት ማሳያ መሆኑን አንስተዋል።

በጤናው ዘርፍ እየተሰሩ የሚገኙ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቅሰው፤ የሆስፒታሉ ባለሙያዎች ህሙማንን በትህትናና  በቅንነት ለማገልገል የጀመሩትን ስራ አጠናክረው እንዲቀጥሉ አስገንዝበዋል።


 

የአስተዳደሩ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ፅጌረዳ ክፍሌ በበኩላቸው ዛሬ ወደ አገልግሎት የተሸጋገረው ማዕከል የጤናን ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ከግብ ለማድረስ እየተሰሩ የሚገኙት ስራዎች መገለጫ መሆኑን ተናግረዋል።

የማዕከሉ ወደ ስራ መግባት በድል ጮራ ሆስፒታል ብቻ ሲሰጥ የነበረውን የህክምና አገልግሎት በማስፋት ጥራትና ፍትሃዊነት ለማረጋገጥ እንደሚያስችል በመግለፅ።

የዚህ አይነቱ ዘመናዊና ደረጃቸውን የጠበቁ አገልግሎቶች ተደራሽ መሆናቸው ድሬዳዋ በኢንዱስትሪና በቱሪዝም ዘርፎች እያከናወነች የምትገኘውን ስራዎች ለማላቅ እንደሚያስችልም አክለዋል።

ማዕከሉ በጤና ሚኒስቴርና በአስተዳደሩ የበጀት ጥምረት ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ በሚሆን ወጪ መገንባቱንም ጠቅሰዋል።

ሆስፒታሉ ፅዱ የጤና ተቋማትን እና ዘመኑን የሚመጥኑ አገልግሎቶች ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን የገለፁት ደግሞ የሳብያን ጠቅላላ ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ ዶክተር ዮናታን ፍቃዱ ናቸው።


 

ሆስፒታሉ  ከህዝቡ የሚነሱ የአገልግሎት ጥያቄዎችን በተገቢው ለመመለስ በትኩረት እየሰራ መሆኑን አንስተው በሆስፒታሉ የተጀመረው  ስራ በስሩ በሚገኙ የገጠርና የከተማው የጤና ተቋማትም ይዳረሳል ብለዋል።

ዛሬ ተመርቆ  ለአገልግሎት ክፍት የሆነው ዘመናዊ የፅኑ ህሙማን ህክምና ማዕከል 10 የህሙማን መታከሚያ አልጋዎች ፣ ዘመናዊ የህክምና መሳሪያዎች እንዲሁም የሰው ኃይል የተሟላለት መሆኑ በወቅቱ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም