ባህላዊ በዓላት የቱሪዝም መስህብና የኢኮኖሚ ምንጭ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቷል - ሚኒስቴሩ - ኢዜአ አማርኛ
ባህላዊ በዓላት የቱሪዝም መስህብና የኢኮኖሚ ምንጭ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቷል - ሚኒስቴሩ

ጌጫ፤ መስከረም 20/2018(ኢዜአ)፦ ህዝባዊ ባህላዊ በዓላት የቱሪዝም መስህብና የኢኮኖሚ ምንጭ ለማድረግ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ።
የሸካቾ ዘመን መለወጫ "ማሽቃሬ ባሮ" በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ሸካ ዞን በተለያዩ ባህላዊ ሥነ ሥርዓቶች እየተከበረ ነው።
በዓሉ በሚከበርበት ጌጫ ከተማ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የባህልና ስፖርት ሚኒስትር አማካሪ ሚኒስትር ዴኤታ ፀጋዬ ማሞ እንዳሉት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የማንነት መገለጫ የሆኑ በዓላት በድምቀት እየተከበሩ ነው።
በተለይ የዘመን መለወጫ በዓላት አከባበር ሥርዓቱ እየተጠናከረ መምጣቱን ገልጸው፣ በመንግስት በኩል በዓላቱን የቱሪዝም መስህብ እና የኢኮኖሚ ምንጭ ለማድረግ እየተሠራ ነው ብለዋል።
ዛሬ እየተከበረ ያለው የሸካቾ ዘመን መለወጫ "ማሽቃሬ ባሮ" ዕሴቱን በጠበቀ መልኩ እንዲጎለብት ሚኒስቴሩ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም ተናግረዋል።
በዓሉ በጋራ ተገናኝቶ በደስታ ከማክበር ባለፈ በውስጡ የያዛቸው ባህላዊ እሴቶች አብሮነትን የሚያጠናክሩ በመሆኑ ለአካባቢው ትልቅ ትርጉም እንዳላቸው ገልጸዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ(ዶ/ር) በክልሉ የሚገኙ ሕዝቦችን ባህልና ታሪክ ለማልማት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
በክልሉ የዘመን መለወጫ በዓላት በአብሮነት መከበራቸው ለሕዝቦች የእርስ በእርስ ትስስርና አንድነት መጠናከር ያላቸው ሚና ጉልህ ነው ሲሉም አክለዋል።
በእርቅና በአብሮነት የሚከበረው የሸካቾ ዘመን መለወጫ በዓል "ማሽቃሬ ባሮ" በትውልድ ቅብብሎሽ ዛሬ ላይ መድረሱንና በጎ የሆኑ ዕሴቶች ጎልተው እንዲወጡ ማስቻሉንም ጠቁመዋል።
በዓሉ የሸካቾን ታሪክና ባህል ለማስተዋወቅ ትልቅ ድርሻ እንዳለው ገልጸው፣ ለእሴቶች ተገቢውን ጥበቃ ማድረግ እንደሚገባም አመልክተዋል።
የሸካ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አበበ ማሞ በበኩላቸው "ማሽቃሬ ባሮ" ክረምት አልፎ በመስከረም ወር የሚከበር፣ የአዲስ ዓመት ተስፋና አብሮነትን የሚያጠናክር የደስታ በዓል ነው ብለዋል።
በበዓሉ ላይ በባህላዊ አስተዳደር ሥርዓት "ምክረቾ" የዓመቱ የሥራ ሁኔታ ተገምግሞ የበረታ ሲመሰገን የደከመ ተሽሮ ሌላ የሚሾምበት በመሆኑ ተግቶ መሥራትን የሚያበረታታ መሆኑን ገልጸዋል።
በሸካ ዞን አንድራቻ ወረዳ ጌጫ ከተማ እየተከበረ ባለው "ማሽቃሬ ባሮ" ላይ የፌዴራል እና የክልል የሥራ ኃላፊዎችና ሌሎች ተጋባዥ የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።