ቀጥታ፡

ጥራቱን የጠበቀ ቡና ለውጭ ገበያ በማቅረብ ገቢን የማሳደግ ተግባር እየተከናወነ ነው

ቡሌ ሆራ፤ መስከረም 20/2018 (ኢዜአ):- ቡናን በጥራት አዘጋጅቶ ለውጭ ገበያ በማቅረብ የዘርፉን ገቢ ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ገለጸ።

የቡሌ ሆራ የቡና ምርት ጥራት ምርመራና ሰርተፊኬሽን ማዕከል ዛሬ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል።


 

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) በወቅቱ እንዳሉት በተያዘው ዓመት ከ600 ሺህ ቶን በላይ ቡና ለውጭ ገበያ በማቅረብ የዘርፉን  የገቢ  አቅም ለማሳደግ ግብ ተጥሎ እየተሰራ ነው።

በዚህም  12 የጥራትና ሰርተፊኬሽን ማዕከል በመገንባት የቡናን ጥራት በማስጠበቅ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ዛሬ ተመርቆ ወደ ስራ የገባው የቡሌ ሆራ የቡና ምርት ጥራት ምርመራና ሰርተፊኬሽን ማዕከል ከእነዚህ ስራዎች አንዱ መሆኑን ጠቅሰው ይህም በጉጂ ዞን የቡና ጥራት  ጠብቆ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ለሚደረገው ጥረት ድርሻው የጎላ ነው ብለዋል።


 

ከዚህ ባለፈም  ቡና  የሚያለሙ  አርሶ አደሮች ምርታቸውን  በተሻለ ዋጋ  ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ድጋፍ እየተደረገ ስለመሆኑም ተናግረዋል።

አዲስ የተከፈተው ማዕከልም የጉጂ ቡና ተፈጥሯዊ ጣዕሙን ጠብቆ ለማዕከላዊ ገበያ እንዲቀርብ የጎላ ሚና እንዳለው ያነሱት ደግሞ የምዕራብ ጉጂ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አዱላ ሕርባዬ ናቸው።

ማእከሉ የአቅራቢዎችን እንግልት በመቀነስ፣ የሥራ እድል በመፍጠርና የከተማውን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች በማነቃቃት ረገድ  ተጨማሪ አቅም  እንዳለውም አክለዋል።

የቡና  ግብይትን በማቀላጠፍ ባለፈው ዓመት ከ85 ሺህ ቶን በላይ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ መቅረቡን አንስተው ተግባሩን በማሳደግም በተያዘው በጀት ዓመት የተሻለ ለማቅረብ ጥረቱ መጠናከሩን ተናግረዋል።

ቡና በመላክ ላይ የሚገኙት አርሶ አደር ኤልያስ ኦዳ በበኩላቸው ማዕከሉ በቅርበት መከፈቱ ልዩ ጣዕም ቡናን በማዘጋጀት የተሻለ ገቢ ለማግኘት እያደረጉ ያለውን ጥረት እንደሚያጠናክር ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም