በአማራ ክልል በበጋው ወቅት ከ383 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ ለማልማት ተግባራዊ እንቅስቃሴ ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል በበጋው ወቅት ከ383 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ ለማልማት ተግባራዊ እንቅስቃሴ ተጀመረ

ባሕርዳር ፤ መስከረም 20/2018 (ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል በዘንድሮው የበጋ ወቅት ከ383 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ ለማልማት ግብ ተይዞ ተግባራዊ እንቅስቃሴ መጀመሩን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
በክልሉ ግብርና ቢሮ የመስኖ እና ሆልቲ ካልቸር ልማት ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክተር አቶ ይበልጣል ወንድምነው ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የምግብ ሉአላዊነትን ለማረጋገጥ ከመኽር እዝመራው ክትትል ጎን ለጎን ለበጋ መስኖ ልማት ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል።
በዘንድሮው የበጋ ወራት ከ1ነጥብ 3 ሚሊዮን የሚበልጡ አርሶ አደሮችን በማሳተፍ 383 ሺህ 686 ሄክታር መሬት ለማልማት የሚያስችል እንቅስቃሴ መጀመሩን አስታውቀዋል።
በበጋ መስኖ በተለያየ የሰብል ዘር ከሚለማው መሬት ውስጥ 260 ሺህ ሄክታሩ በስንዴ የሚለማ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
የመስኖ ልማቱ የሚከናወነው በአርሶ አደሩ እጅ የሚገኙ ከ68 ሺህ የሚበልጡ የውሃ መሳቢያ ቴክኖሎጂዎችንና የመስኖ ግድቦችን በመጠቀም እንደሆነ አስረድተዋል።
በዚህም እንደቲማቲም፣ ሽንኩርትና በርበሬ የመሳሰሉ የአትክልት ችግኞችን የማዘጋጀት ተግባርም ከወዲሁ ትኩረት ተሰጥቶት እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።
በመስኖ ልማቱም ፈጥነው የሚደርሱ የአትክልትና የተለያዩ የሰብል ዝርያዎችን ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ዙር በማልማት ከ52 ነጥብ 3 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን አቶ ይበልጣል አስታውቀዋል።
በሰሜን ጎጃም ዞን የሰሜን ሜጫ ወረዳ አርሶ አደር እንየው ሙሉ በሰጡት አስተያየት፤ የዝናብ ወቅትን ሳይጠብቁ በበጋ መስኖ ሰብሎችን በማልማት የምግብ ዋስትናቸውን ለማረጋገጥ እንዳገዛቸው ገልጸዋል።
በዘንድሮው የበጋ ወራት ከግማሽ ሄክታር በሚበልጥ ማሳቸው ስንዴ፣ ሽንኩርት፣ ቲማቲምና ቃሪያ ለማልማት ከወዲሁ ወደ ተግባር መግባታቸውን ገልጸዋል።
በደቡብ ጎንደር ዞን የደራ ወረዳ አርሶ አደር መልኬ መንግስቴ ፤ አንድ ሄክታር የሚጠጋ ማሳቸውን በዓመቱ እስከ ሁለት ጊዜ ለማልማት እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
የውሃ መሳቢያ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ሽንኩርት፣ ቲማቲም ቃሪያና ስንዴ ሰብል በማልማት ከራሳቸው ፍጆታ የሚተርፈውን ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ ማቀዳቸውን አመልክተዋል።
የግብርና ቢሮ መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በአማራ ክልል ባለፈው ዓመት የበጋ ወራት በመስኖ ከለማው 331ሺህ ሄክታር መሬት ከ46 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ተገኝቷል።