በአሪ ዞን በተያዘው የመኸር አዝመራ አራት ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይጠበቃል - ኢዜአ አማርኛ
በአሪ ዞን በተያዘው የመኸር አዝመራ አራት ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይጠበቃል

ጂንካ፤መስከረም 20/2018(ኢዜአ) :- በአሪ ዞን በዘንድሮ የመኸር አዝመራ የምርት ማሳደጊያ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ወደ አራት ሚሊዮን ኩንታል የሚጠጋ ምርት ለማግኘት እየተሰራ መሆኑን የአሪ ዞን ግብርና መምሪያ አስታወቀ ።
ዞኑ ደጋ፣ ወይናደጋ እና ቆላማ የአየር ፀባይ ያለው ሲሆን በርካታ የከርሰ ምድርና የገፀ-ምድር የውሃ ሀብቶችና ለም መሬቶች በስፋት የሚገኝበት አካባቢ ነው።
በመምሪያው የእርሻ ዘርፍ ኃላፊ ተወካይ መልካሙ ሙሐመድ፥ በአካባቢው ያለውን ዕምቅ የግብርና አቅም አሟጦ በማልማት የሰብል ምርታማነትን ለማሳደግና በምግብ ራስን ለመቻል ጥረት እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።
በተያዘው የመኸር አዝመራ በዞኑ 40 ሺህ ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑን ገልጸው፣ የምርት ማሳደጊያ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም አራት ሚሊዮን ኩንታል የሚጠጋ ምርት ለማግኘት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በእርሻ ሥራው ከ148 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች ተሳታፊ መሆናቸውን ገልጸው በዋናነት በቆሎ፣ ማሽላ፣ ስንዴና ገብስ እየለሙ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የአሪ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ጉራልቅ ይዥማልቅ በበኩላቸው በዞኑ በመኸር እርሻ በአጠቃላይ እየለማ ካለው መሬት 11 ሺህ ሄክታሩ በምርጥ ዘር እየለማ መሆኑን ጠቁመዋል።
"ቢ ኤች 140 እና መልካሳ-2" የተሰኙ የተሻሻሉ የበቆሎና የማሽላ ሰብል ዝርያዎችን በማባዛት በዞኑ ያለውን የምርጥ ዘር እጥረት ችግር ለመፍታት በስፋት እየተሰራ መሆኑንም አክለዋል።
በቀጣይም የዘር ብዜት ሥራውን በጥናትና ምርምር በማገዝና በማስፋፋት ለተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ምርጥ ዘርን በስፋት ለማቅረብ ትኩረት መደረጉን ገልጸዋል።
የዞኑ አርሶ አደሮች በበኩላቸው በኩታ ገጠም እርሻ እያለሙት ላለው የበቆሎ እና የማሽላ ማሳ ተገቢ እንክብካቤ እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በዞኑ ባካዳውላ አሪ ወረዳ የኩሬ ቀበሌ አርሶ አደር መልካሙ አንክሺ፥ በመኸር እርሻ በሁለት ሄክታር መሬት ላይ እያለሙት ካለው ሰብል የተሻለ ምርት ለማግኘት እየሰሩ መሆኑን ጠቁመዋል።
በግብርና ባለሙያዎች ምክረ ሀሳብ መሰረት የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በሙሉ ፓኬጅ በመጠቀም ልማቱን እያከናወኑ መሆናቸውን ጠቅሰው፥ በዚህም ምርታማነታቸው በእጥፍ እያደገ መሆኑን ተናግረዋል።
ሌላው የቀበሌው አርሶ አደር አዲሱ አንግሪ በበኩላቸው የመኸር ወቅት የአየር ጸባይ ለልማት ስራቸው ምቹና የተስተካከለ እንደነበር አንስተዋል።
ከመኸር አዝመራው ጎን ለጎን አሁን እየጣለ ያለውን ዝናብ ለበጋ እርሻ ማሳቸው ለመጠቀም አነስተኛ ኩሬ በመስራት ውሃ እያሰባሰቡ መሆኑንም ገልጸዋል።