ኢሬቻ አብሮነት የሚጸናበት እና አሰባሳቢ ትርክት የሚጎለብትበት በዓል ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢሬቻ አብሮነት የሚጸናበት እና አሰባሳቢ ትርክት የሚጎለብትበት በዓል ነው
አዲስ አበባ፤ መስከረም 20/2018 (ኢዜአ)፡-ኢሬቻ አብሮነት የሚጸናበት እና አሰባሳቢ ትርክት የሚጎለብትበት በዓል መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አመራሮች ገለጹ።
የ2018 የኢሬቻ በዓል " ኢሬቻ ለሀገር ማንሰራራት " በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ በክፍለ ከተማ ደረጃ በአራዳ ክፍለ ከተማ እየተከበረ ይገኛል።
የምስጋና በዓል የሆነው ኢሬቻ ከክረምት ወቅት መለያየትና መራራቅ በኋላ ሰዎች በአብሮነት ብርሃን ለማየት ያበቃቸውን ፈጣሪ የሚያመሰግኑበት በዓል መሆኑም በዚሁ ወቅት ተገልጿል።
ኢሬቻ ስለአንድነት የሚዘመርበት፣ ስለመጪው ጊዜ መልካም ምኞት የሚገለጽበት፣ አብሮነት የሚጸናበት በዓል መሆኑም እንዲሁ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አብርሃም ታደሰ በዚሁ ወቅት፤ ኢሬቻ የሰላምና የወንድማማችነት ምልክት ነው ብለዋል።
ኢሬቻ የሰው ልጅ ከተፈጥሮ ጋር ያለው ጥብቅ ግንኙነት የሚገለጽበት እንዲሁም የኢትዮጵያን ማንሠራራት ዕውን ለማድረግ ህብረት የሚፈጠርበት በዓል መሆኑን ተናግረዋል።
የኢሬቻ በዓል እሴቶችን ለሀገር ማንሠራራትና ሁለንተናዊ ብልጽግና ማዋል እንደሚገባም ጠቁመዋል።
በዓሉ ሀገር ከተስፋ ብርሃን ወደሚጨበጥ ብርሃን በተሸጋገረችበት ወቅት መከበሩ ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።
የአራዳ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ጌታሁን አበራ፤ የኢሬቻ በዓል ከገዳ ስርዓት ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያለው ለፈጣሪ ምስጋና የሚቀርብበት፣ ሠላምና ፍቅር የሚጸናበት በዓል ነው ብለዋል፡፡
በዓሉን ስናከበር ህብረ-ብሔራዊ አንድነታችንን ይበልጥ በማጠናከር ብሎም ሀገራችንን በመጠበቅና ልማታችንን በማስቀጠል ሊሆን እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
የኢሬቻ በዓልን ስናከብር የብሔራዊነት አሰባሳቢ ትርክትን በማጉላት መሆን እንዳለበትም ጠቁመዋል።
የበዓሉ ታዳሚዎች ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ኢሬቻ የአብሮነት እሴት መገለጫ፣ የአንድነትና የሰላም በዓል ነው ብለዋል፡፡
አባገዳ ሁሴን ቂጤሳ እንዳሉትም ኢሬቻ ሁሉም በጋራ የሚያከብረው የፍቅር፣ የአንድነት እና የአብሮነት በዓል መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ወይዘሮ አልማዝ ድሪባ በበኩላቸው ኢሬቻ ህዝቡ በአንድነት በመሆን ለፈጣሪ ምስጋና የሚያቀርብበት እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡
ኢሬቻ በህብረት የሚከበር የአደባባይ በዓል እንዲሁም ፍቅር እና አብሮነት የሚገለጽበት በዓል መሆኑን የገለጸው ደግሞ ወጣት ኤሊያስ ጀማል ነው፡፡