ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ግዙፍ የልማት ዕቅዶች የሀገርን ሁለንተናዊ እድገት ለማረጋገጥ ጉልህ ድርሻ ይኖራቸዋል

አዲስ አበባ፤ መስከረም 20/2018 (ኢዜአ)፡-በህዳሴ ግድብ ምርቃት ላይ የተበሰሩት የኢትዮጵያ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክት ዕቅዶች የሀገርን ሁለንተናዊ እድገት ለማረጋገጥ ጉልህ ድርሻ እንደሚኖራቸው የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጳጉሜን 4 ቀን 2017 ዓ.ም በህዳሴ ግድብ ምርቃት ላይ በ30 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ወጪ የሚገነቡ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክት ዕቅዶችን ማብሰራቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ የልማት ፕሮጀክት ዕቅዶችም ሰላማዊ የኒውክሌር ማብላያ፣ የነዳጅ ዘይት ማጣሪያ፣ የተፈጥሮ ጋዝ ፋብሪካ፣ ግዙፍ የአየር ማረፊያ፣ የ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ቤቶችና የማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ ይገኙበታል።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ ለኢዜአ እንዳሉት÷  የህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ ብልጽግና ማብሰሪያ የሀገር ማንሰራራት መገለጫ ለመሆን በቅቷል።

ኢትዮጵያዊያን ለግድቡ የግንባታ ሂደት በሁሉም መስክ በኅብር ያበረከቱት አስተዋጽኦም የቅድመ አያቶችን የመቻል መንፈስ የገለጠ አኩሪ የልማት ገድል መሆኑን ገልጸዋል።

የህዳሴ ግድብ የሚያመነጨው የኃይል አቅርቦትም ኢትዮጵያ በሁሉም መስክ  እያስመዘገበች የምትገኘውን የልማት ስኬት ለማሳለጥ ወርቃማ ዕድል ይዞ መምጣቱን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የመቻል ሀገር ናት ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው÷ በዚህም በትውልድ ቅብብሎሽ አክሱምና ላሊበላን ያነጸ በዓድዋ ተራሮች ወራሪን ድል የነሳ ታሪክ ቀያሪ ትውልድ የሚነሳባት ሀገር መሆኗን አንስተዋል። 

የአሁኑ ትውልድም በታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የፈጸመው አኩሪ የልማት ገድል አኩሪ ኅብረ-ብሔራዊ አንድነትን የሚያንጽ ደማቅ ትርክት መፃፍ እንደቻለ አብራርተዋል። 

ኢትዮጵያዊያንም አደባባይ በመውጣት የህዳሴ ግድብ መጠናቀቅን አስመልክቶ በከፍተኛ የደስታ ስሜት ማክበራቸውን አስታውሰዋል።

የህዳሴ ግድብ ተጠናቆ ለምርቃት መብቃቱም ተጨማሪ ግዙፍ ብሔራዊ የልማት ዕቅድ ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ ለማድረግ  መነሻ ሆኖ የሚያገለግል መሆኑን ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በህዳሴ ግድብ ምርቃት ላይ ያበሰሯቸው የ30 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ ጉልህ ድርሻ ይኖራቸዋል ብለዋል።

በቀጣይ የሚገነቡ ግዙፍ ፕሮጀክቶችም መሠረተ ልማትን በማሟላት፣ የኃይል አቅርቦትን ለማሳደግ፣ የግብርና ምርታማነትን ለማላቅ የማይተካ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ አብራርተዋል። 

መንግስትም የኢትዮጵያን የዕድገትና ብልጽግና ጉዞ በማሳለጥ የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የልማት ስራዎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

የሰላማዊ የኒውክሌር ማብላያ፣ የነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ፋብሪካ፣ የአየር ማረፊያ፣  የማዳበሪያ ፋብሪካና መሰል የልማት ግንባታዎችም የዕድገት ከፍታን ለማፅናት ትርጉም የሚሰጣቸው እንደሆኑ አንስተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም