ቀጥታ፡

ኢሬቻ ማህበራዊ ትስስርን ማጠናከሪያ መድረክ እየሆነ መጥቷል  -አቶ ሃይሉ አዱኛ

አዳስ አበባ ፤ መስከረም 20/2018 (ኢዜአ)፡- የኢሬቻ በዓል ማህበራዊ ትስስርን የማጠናከሪያ አንዱ መድረክ እየሆነ መምጣቱን የኦሮሚያ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ሃይሉ አዱኛ ተናገሩ።

በክልሉ ፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት እና ኮሙኒኬሽን ቢሮ ትብብር "ኢሬቻ ለሀገር ማንሰራራት" በሚል መሪ ሀሳብ የሚከበረውን የዘንድሮ ኢሬቻ በዓል ላይ ያተኮረ 'ጉሚ በለል' የውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው።


 

በውይይት መድረኩ ላይ የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ሃይሉ አዱኛ፣ የክልሉ ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ጀሚላ ሲምብሩ፣ አባ ገዳዎች፣ ሃዳ ሲንቄዎች እና ምሁራን ተገኝተዋል።

የውይይት መድረኩን የከፈቱት አቶ ሃይሉ እንዳሉት የገዳ ስርዓት አንዱ አካል የሆነው ኢሬቻ በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ በትልቁ የሚከበር በዓል ነው።

በዓሉ ህዝቡ ያለ ልዩነት በአንድነት ወጥቶ ጨለማውን የክረምት ወራት በማለፉ ለፈጣሪው ምስጋና የሚያቀርብበት መሆኑን አንስተዋል።

እንዲሁም በዓሉ ፍቅር፣ ሰላምና አንድነት የሚንጸባረቅበት ሆኖ ለመጪው ጊዜ ተስፋ የሚሰነቅበት መሆኑንም ተናግረዋል።


 

ኢሬቻ በርካታ በጎ እሴቶች ያሉት መሆኑን ያነሱት አቶ ሃይሉ፤ ኢሬቻ ማህበራዊ ትስስርን ማጠናከሪያ መድረክ እየሆነ መጥቷል ብለዋል።

ይህም በመሆኑ የአሁኑ ትውልድ ኢሬቻን የመሰሉ በጎ ማህበራዊ እሴቶችን መጠበቅ እና ማሳደግ አለበት ብለዋል።

የዘርፉ ምሁራንም የኢሬቻን ምንነትና ትክክለኛ መገለጫዎችን በጥናትና ምርምር በማስደገፍ ማሳወቅ እና ማስገንዘብ እንዳለባቸው አስረድተዋል።

በመድረኩ ላይ የውይይት መነሻ ጽሁፍ ያቀረቡት በአርሲ ዩኒቨርሲቲ የገዳ ትምህርት መምህር የሆኑት መሐመድ ነሞ (ዶ/ር) ኢሬቻ የወንድማማችነት እና እህትማማችነት ማጠናከሪያ በዓል ነው ብለዋል።

የኢሬቻ በዓል ሰላምና መተማመንን የሚያጠናክር መሆኑን ገልጸዋል።


 

ኢሬቻን የመሰሉ በዓላት ለሀገር ግንባታ እና ለህብረ ብሔራዊ አንድነት መጠናከር ያላቸው ፋይዳ ትልቅ መሆኑን አንስተዋል።

የዘንድሮው ኢሬቻ በዓል የፊታችን ቅዳሜ እና እሁድ በሆረ ፊንፊኔ እና በሆረ አርሰዲ እንደሚከበር ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም