የ15 ጊዜ የሻምፒዮንስ ሊግ አሸናፊው ሪያል ማድሪድ በሻምፒዮንስ ሊጉ ከካይራት አልማቲ ጋር ይጫወታል - ኢዜአ አማርኛ
የ15 ጊዜ የሻምፒዮንስ ሊግ አሸናፊው ሪያል ማድሪድ በሻምፒዮንስ ሊጉ ከካይራት አልማቲ ጋር ይጫወታል

አዲስ አበባ፤ መስከረም 20/2018(ኢዜአ)፦ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ሁለተኛ መርሃ ግብር ሪያል ማድሪድ ከካዛኪስታኑ ካይራት አልማቲ ጋር ዛሬ ጨዋታውን ያደርጋል።
የክለቦቹ ጨዋታ ምሽት 1 ሰዓት ከ45 ላይ በኦርታሊክ ስታዲየም ይካሄዳል።
ሪያል ማድሪድ በመጀመሪያ ጨዋታው ማርሴይን 2 ለ 1 ሲረታ፣ ካይራት አልማቲ በስፖርቲንግ ሊዝበን 4 ለ 1 ተሸንፏል።
ሁለቱ ክለቦች በሻምፒዮንስ ሊጉ ሲገናኙ የአሁኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
የ15 ጊዜ የውድድሩ አሸናፊ ሪያል ማድሪድ ጨዋታውን ለማድረግ ሰባት ሺህ ኪሎ ሜትር ገደማ ያደረገው የአውሮፕላን ጉዞ መነጋገሪያ ሆኗል። ጉዞው በተጫዋቾቹ አካላዊ ዝግጁነት ላይ ተጽእኖ እንደሚያሳድር እየተነገረ ይገኛል።
በተመሳሳይ ከምሽቱ 1 ሰዓት ከ45 ላይ አትላንታ ከክለብ ብሩዥ ይጫወታሉ።
ምሽት 4 ሰዓት ላይ ሰባት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።
ቼልሲ ከቤኔፊካ፣ ጋላታሳራይ ከሊቨርፑል፣ ፓፎስ ከባየር ሙኒክ፣ አትሌቲኮ ማድሪድ ከኢንትራክት ፍራንክፈርት፣ ኢንተር ሚላን ከስላቪያ ፕራግ፣ ማርሴይ ከአያክስ እና ቦዶ ግሊምት ከቶተንሃም ሆትስፐርስ ይጫወታሉ።