ቀጥታ፡

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ስኬት የመድኃኒትና የሕክምና መገልገያ አምራቾችን የምርታማነት አቅም ያሳድጋል

አዲስ አበባ፤ መስከረም 20/2018 (ኢዜአ)፡- የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ስኬት የሕክምና መገልገያ አምራቾችን የምርታማነት አቅም በማሳደግ ኢትዮጵያን የመድሃኒት ምርት ማዕከል ለማድረግ የሚያስችል መሆኑን የኢትዮጵያ መድኃኒትና የሕክምና መገልገያ አምራች ዘርፍ ማኅበር አስታወቀ።

የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብዱልቃድር ገልገሎ ለኢዜአ እንዳሉት÷ የዜጎችን የመድኃኒትና ሕክምና መገለገያ የተደራሽነት ፍላጎት ለማሻሻል እየተሰራ ነው ብለዋል።


 

ባለፉት ዓመታትም ለጤና ዘርፍ መሻሻል የተወሰዱ የሕግና የፖሊሲ እርምጃዎች የሀገር ውስጥ የመድኃኒት ምርታማነት አቅምን በማሳደግ በተኪ ምርት አበረታች ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል።

በዚህም የፋርማሲቲካል ኢንዱስትሪዎችም ከውጭ የሚገቡ የመድኃኒትና የሕክምና መገልገያ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት 41 በመቶ የገበያ ድርሻን መያዝ ያስቻለ ስኬት ማስመዝገባቸውን ተናግረዋል።  

የመድኃኒትና የሕክምና መገልገያ የፋርማሲቲካል አምራች ኢንዱስትሪዎችን የምርታማነት አቅም በማሳደግ የአቅርቦት ፍላጎት ተደራሽነትን ለማሳደግ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ተጠናቆ ወደኃይል አቅርቦት መሸጋገሩ የመድኃኒትና የሕክምና መገልገያ አምራቾችን የምርታማነት አቅም በማሳደግ ተደራሽነትን ለማስፋት ትልቅ ብስራት መሆኑን ገልጸዋል።

የህዳሴ ግድብ የኃይል አቅርቦትም በፋርማሲቲካል ኢንዱስትሪ መሰማራት የሚፈልጉ የውጭ አልሚዎችን የኢንቨስትመንት ፍላጎት በማሳደግ መልካም ዕድል ይዞ መምጣቱን ተናግረዋል።

በፋርማሲተካል ኢንዱስትሪ የሚሰማሩ አልሚ ባለሃብቶችም የመድኃኒትና የሕክምና መገልገያ ምርታማነት አቅምን በማሳደግ ከሀገር ውስጥ ባለፈ ለውጭ ንግድና የስራ ዕድል ፈጠራ ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ መድኃኒትና የሕክምና መገልገያ አምራች ዘርፍ ማኅበር ፕሬዝዳንት ዶክተር ታደሰ ተፈሪ÷ በጤናው መስክ የተወሰዱ እርምጃዎች ዘርፉ እመርታዊ ለውጥ እንዲያስመዘግብ አስችሎታል ብለዋል።


 

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ተጠናቆ ኃይል ወደማምረት መሸጋገሩ የኃይል አቅርቦት ፍላጎትን በመጨመር የመድኃኒትና የሕክምና መገልገያ የምርታማነት አቅም ለማሳደግ ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው መሆኑን ገልጸዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ስኬት ኢትዮጵያን የመድሃኒት ምርት ማዕከል ለማድረግ የይቻላል መንፈስን የፈጠረ መሆኑን ገልጸው፤ በዚህ ረገድ የግሉን ዘርፍ የሚያበረታታ ነው ብለዋል። 

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የምስራቅ አፍሪካና የካረቢያን ሀገራት መሪዎች በተገኙበት ጳጉሜን 04 ቀን 2017 ዓ.ም ለምርቃት መብቃቱ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም