ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በታሪካዊ፣ ባህላዊ እና ተፈጥሯዊ መዳረሻዎች የታደለች ሃገር ናት- የውጭ ሀገራት ጎበኚዎች 

አዲስ አበባ፤ መስከረም 20/2018 (ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ የጎብኚዎችን ቀልብ የሚስቡ ታሪካዊ፣ ባህላዊና ተፈጥሯዊ መዳረሻዎች ያሏት ሀገር መሆኗን ኢዜአ ያነጋገራቸው የውጭ ሀገራት ጎበኚዎች ገለጹ።

ኢትዮጵያ ያሏትን እምቅ የተፈጥሮና ታሪካዊ ቅርሶች ለመጎብኘት በየዓመቱ ከአንድ ሚሊዮን የላቁ የውጭ ሀገር ዜጎች ወደ አገሪቱ ይተማሉ፡፡

ጎብኚዎቹ በአብዛኛው በዩኔስኮ የተመዘገቡ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ እንዲሁም በምዝገባ ሂደት ላይ ያሉ ሰው ሰራሽና ባህላዊ ቅርሶችን መጎብኘት ደግሞ ምርጫቸው ነው፡፡

ኢትዮጵያን ለመጎብኘት ለሁለተኛ ጊዜ ሀገሪቱን የረገጡት አሜሪካዊት ቱሪስት ማርኪያ ዳርም በመጀመሪያ ጉብኝታቸው የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን፣ የጥምቀት በዓል አከባበርንና የኦሞ ሸለቆን መመልከታቸውን አስታውሰዋል፡፡


 

ኢትዮጵያን ከረገጡበት ቀን አንስቶ የተመለከቱት የማህበረሰቦች ባህልና እሴት እንዲሁም የማይረሳ መስተንግዶ በድጋሚ እንዲመጡ እንዳነሳሳቸው ተናግረዋል፡፡

በቀደመ ቆይታቸው ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ ባህል፣ ታሪክ፣ ቅርስና የተፈጥሮ መስህብ መመልከታቸውን ጠቅሰዋል፡፡

አውስትራሊያዊው ኒክ ድን በበኩላቸው በኢትዮጵያ በነበራቸው የቆይታ ጊዜ የኦሞ ሸለቆና ሌሎች መዳረሻዎችን መመልከታቸውን ገልጸዋል፡፡ 


 

በጎበኟቸው አካባቢዎች አስደናቂ የማህበረሰብ አኗኗር፣ ባህልና እሴት በመመልከት የማይረሳ ልምድ መቅሰማቸውን ተናግረዋል፡፡

ስፔናዊው ፓብሎ ዊድን እንደገለጹት በኢትዮጵያ ዓይን የሚማርኩ፣ የውስጥ እርካታ የሚሰጡና መንፈስን የሚያድሱ ባህላዊና ታሪካዊ የተፈጥሮ መስህቦችን ጎብኝተዋል፡፡


 

ጎብኝዎቹ ኢትዮጵያ እምቅ የሆነ ታሪካዊ፣ ባህላዊና ተፈጥሯዊ የቱሪስት መዳረሻ የታደለች ሀገር መሆኗን ገልጸዋል፡፡

በአዲስ አበባ የተለያዩ የቱሪስት መዳረሻዎች መኖራቸውን ጠቅሰው በተለይ በኢትዮጵያ ብሔራዊ  ሙዚዬም በአፍሪካ ብሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፅዕኖ ያላቸው ቅርሶች፣ ቅሪተ አካላትና የጥናት ግኝቶች መኖራቸውን ጎብኝዎቹ ገልጸዋል፡፡ 

ነዋሪነታቸውን በአሜሪካ ያደረጉት ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ወይዘሮ ወርቅነሽ ዘውዴ ዘወትር ወደ ሀገራቸው ሲመጡ አዲስ ስሜት እንደሚፈጠርባቸው ገልጸዋል፡፡


 

ኢትዮጵያ የተለያዩ ቅርሶች፣ታሪኮች ባህሎችና የተለየ የአየር ጸባይ የተላበሰች ውብ ሀገር መሆኗን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም