የአዝርዕት ዝርያዎችን በምርምር በማሻሻል ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሠራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአዝርዕት ዝርያዎችን በምርምር በማሻሻል ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሠራ ነው
አዲስ አበባ፤ መስከረም 20/2018 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ብዝኀ ሕይወት ኢንስቲትዩት የአዝርዕት ዝርያዎችን በምርምር በማሻሻል ምርትና ምርታማነትን ይበልጥ ለማሳደግ በትኩረት እየሠራ መሆኑን አስታወቀ።
በኢንስቲትዩቱ የአዝርዕትና ሆርቲካልቸር ምርምር መሪ ሥራ አስፈጻሚ ውብሸት ተሾመ ለኢዜአ እንዳሉት፤ እስካሁን የተደረሰባቸው እና የተመዘገቡ 89 ዓይነት የአዝርዕት ዝርያዎች እና 92 ሺህ ናሙናዎች አሉ።
ከእነዚህ መካከል 12 ዓይነት የአዝርዕት ዝርያዎች በኢትዮጵያ ብቻ እንደሚገኙም አረጋግጠዋል።
የአዝርዕት ዓይነቶቹና ናሙናዎቹ በመስክና በማቀዝቀዣ ክፍል ጥበቃ እየተደረገላቸው መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም መሠረት ገብስ፣ ጤፍ፣ ሽምብራ፣ ተልባ፣ ድንብላል፣ አብሽ እና ሌሎች የአዝርዕት ዓይነቶችን ምርታማነታቸውን ለማሳደግ ኢንስቲትዩቱ በምርምር እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
እስካሁን ድረስም በሽታ እና ድርቅ የሚቋቋም በሔክታር እስከ 58 ኩንታል ምርት መስጠት የሚችል አራት ዓይነት የስንዴ ዝርያ በምርምር መሻሻሉን ተናግረዋል።
ከተሻሻለው የስንዴ ዝርያ 200 ኩንታል ዘንድሮ ለአርሶ አደሩ ተሠራጭቶ መዘራቱን ጠቅሰው፤ 70 ኩንታል ደግሞ በማኅበራዊ ዘር ባንክ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
በምርምር ከተሻሻለው አራት ዓይነት የስንዴ ዝርያ ጋር በተያያዘ ቀሪው ሥራ በግብርና ባለስልጣን አማካኝነት የዝርያ ማስመዝገብና ቀሪ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።
ገብስ እና ጤፍን ጨምሮ ሌሎች የአዝርዕት ዓይነቶች በምርምር ሂደት ላይ እንደሚገኙም አመላክተዋል።
በአጠቃላይ የሰብል ዝርያዎችን በምርምር የማሻሻሉ ተግባር ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ እንደ ሀገር የተያዘውን የምግብ ዋስትና የማረጋገጥ ሂደት በእጅጉ ያግዛል ነው ያሉት።
ከሆርቲካልቸር አኳያም ሥራሥር፣ እንሰት፣ ቅመማቅመምን ጨምሮ በአምስት የመስክ ጂን ባንኮች 9 ሺህ ያህል ናሙናዎች ጥበቃ እየተከናወነ ነው ብለዋል።
ለአብነትም ከ6 ሺህ በላይ የቡና ናሙና በመስክ የጂን ባንክ ጥበቃ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።