የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክን በማልማትና በመጠበቅ የሚገኘውን ገቢ ይበልጥ ለማሳደግ የተጀመሩ ሥራዎች ይጠናከራሉ - ኢዜአ አማርኛ
የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክን በማልማትና በመጠበቅ የሚገኘውን ገቢ ይበልጥ ለማሳደግ የተጀመሩ ሥራዎች ይጠናከራሉ
ሮቤ፤ መስከረም 19/2018 (ኢዜአ)፡-ዓለም አቀፍ ቅርስ የሆነው የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በማልማትና በመጠበቅ የሚገኘውን ገቢ ይበልጥ ለማሳደግ የተጀመሩ ሥራዎች ሊጠናከሩ እንደሚገባ ተመለከተ፡፡
በኦሮሚያ ክልል ባሌ ዞን ''ቱሪዝም እና ለውጥ'' በሚል መሪ ሃሳብ የዓለም የቱሪዝም ቀን በተለያዩ መርሃ ግብሮች ተከብሯል።
በዚሁ መሰረትም የዘርፉ የሥራ ኃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ አካል የሆነውን የሳነቴ አምባና ሌሎች አካባቢዎች ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
በጉብኝታቸውም የበርካታ ብርቅዬ አራዊትና አዕዋፋት ባለቤት የሆነውን የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የማየት እድል በማግኘታቸው መደሰታቸውን ተናግረዋል።
ከጉብኝቱ ተሳታፊዎች መካከል የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ነጋሽ፤ ፓርኩ የበርካታ ብርቅዬ የዱር እንስሳትና አእዋፋት መገኛ የሆነ ድንቅ ስፍራ በመሆኑ ተጠብቆ ለትውልድ መተላለፍ ያለበት የሀገር ሃብት ነው ብለዋል።
ፓርኩ በውስጡ የተለያየ ስነ-ምህዳር በአንድ ቦታ በማቀፉ ''አንድ ፓርክ ብዙ ዓለም'' የሚል ስያሜ ማግኘቱን በጉብኝታቸው ወቅት በተጨባጭ ማረጋገጣቸውንም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን ምክትል ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን መኮንን፤ በበኩላቸው ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በብሔራዊ ፓርኮች ላይ የሚፈጸሙ ሰው ሰራሽ አደጋዎችን ለመከላከል ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይ በፓርኮች ዙሪያ የእርሻ መስፋፋት፣ የደን ምንጣሮ፣ ልቅ ግጦሽ፣ ሰደድ እሳት፣ ሕገ ወጥ አደንና መሰል ተግባራት እንዳይባባሱ እየተሰራ ነው ብለዋል።
የፓርኮችና የሌሎች የተፈጥሮ ሃብቶች ጥበቃ በተወሰኑ አካላት ኃላፊነት ብቻ ማሳካት አይቻልም ያሉት አቶ ሰለሞን የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ሊጠናከር እንደሚገባም አሳስበዋል።
በዞኑ የሚገኙ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ መስህቦችን ይበልጥ እንዲተዋወቁና መሠረተ ልማትን ለማሟላት የተጀመሩ ጥረቶች የሚደነቁ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ ወደ ፓርኩ ለመጀመርያ ጊዜ የመጡትና የሆቴል ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ባልደረባ አቶ ሜሎር ረድኢ ናቸው።
በተለይም ወደ መዳረሻዎቹ የሚወስዱ የመንገድ መሰረተ ልማትና የሎጅ አገልግሎትን ማሟላት የቱሪስት ቆይታን በማራዘም ከዘርፉ የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማሳደግ እንደሚያግዝም አክለዋል።
የብሔራዊ ፓርኩ ኃላፊ አቶ ሻሚል ከድር በበኩላቸው በዓለም ቅርስነት የተመዘገበው የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የደጋ አጋዘን፣ ቀይ ቀበሮ፣ ድኩላ፣ የባሌ ጦጣና የሌሎች የዱር እንስሳትና አዕዋፋት መገኛ ስለመሆኑ አንስተዋል።
በፓርኩ አካባቢ የሚስተዋሉትን ሰው ሰራሽ ተግዳሮችን በማስወገድና የመሰረተ ልማት ችግሮችን በመፍታት ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ ትኩረት መደረጉን አመልክተዋል።
የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በ45ኛው የዓለም ቅርስ ጉባኤ ላይ በዓለም ቅርስነት በቋሚነት መመዝገቡ ይታወሳል።