የሆረ አርሰዲ ኢሬቻ በዓል እሴቱን በጠበቀ መልኩ ለማክበር የሚያስችል ዝግጅት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
የሆረ አርሰዲ ኢሬቻ በዓል እሴቱን በጠበቀ መልኩ ለማክበር የሚያስችል ዝግጅት ተደርጓል
ቢሾፍቱ፤ መስከረም 19/2018 (ኢዜአ)፦ በቢሾፍቱ የሚከበረውን የሆረ አርሰዲ ኢሬቻ በዓል ሰላማዊነቱንና እሴቱን በጠበቀ መልኩ ለማክበር የሚያስችል ዝግጅት መደረጉን የከተማ አስተዳደሩ ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
የዘንድሮው ኢሬቻ በዓል መስከረም 24 እና 25 በበሆረ ፊንፊኔ እና ሆረ አርሰዲ የሚከበር ሲሆን በዓሉን የተሻለ ለማድረግ ባለድርሻ አካላት የተለያየ ዝግጅት እያደረጉ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሪፖርተርም በቢሾፍቱ ሆረ አርሰዲ የሚከበረውን ኢሬቻ በዓል በተመለከከተ በከተማ አስተዳደሩ እየተደረገ የሚገኘውን ዝግጅት ቃኝቷል።
የከተማ አስተዳደሩ ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ገነት መኮንን እንዳሉት በዓሉ እሴቱን በጠበቀ መልኩ ለማክበር ዝግጅት ተደርጓል።
ከተማ አስተዳደሩ ከዚህ በፊት የቀመረውን መልካም ተሞክሮ በመጠቀም የዘንድሮውን የተሻለ ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል።
ከነዚህም ዝግጅቶች መካከል ከተማዋን በዓሉ ላይ ለሚታደሙ እንግዶች ምቹ ማድረግ አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚህም የከተማዋን ዋና ዋና መንገዶች የማስፋት እና ለንግድ እንቅስቃሴ የተመቸ የማድረግ ስራ መሰራቱን ተናግረዋል።
በተለይም ዘንድሮ በሆረ አርሰዲ ላይ የሚታደሙ እንግዶች እና የውጭ አገር ቱሪስቶች ሃይቁን ተዘዋውረው የሚጎበኙበት የቀለበት መንገድ መገንባቱን ገልጸዋል።
አጠቃላይ ለበዓሉ መንገዶችን የማስፋት፣ መብራት የመግጠም እና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አቅማቸውን እንዲያጠናክሩ የማድረግ እንዲሁም ሌሎች የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ተከናውነዋል ብለዋል።
የከተማው ነዋሪና የአገር ሽማግሌው አዲሱ በልዳ እንዳሉት የኢሬቻ በዓል በክረምቱና በወንዝ ሙላት ምክንያት ተራርቀው የቆዩ ዘመድ አዝማድ እና ወዳጆች በናፍቆት የሚገናኙበት ነው።
ሆረ አርሰዲ ሁሉም ከየአካባቢው ተሰባስቦና በባህል ልብስ አጊጦ በመገኘት ለፈጣሪው ምስጋና የሚያቀርብበት በናፍቆትና በጉጉት የሚጠበቅ በዓል መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም የዘንድሮው የኢሬቻ በዓል እሴቱን በጠበቀ መልኩ እንዲከበር የሚጠበቅባቸውን ሁሉ እያደረጉ መሆኑን አስረድተዋል።
ሃደ ሲንቄ አስናቁ ቱፋ በበኩላቸው ኢሬቻ በርካታ ሰዎች የሚታደሙበት ደማቅ በዓል መሆኑን ጠቅሰው በዓሉ የተሳካ እንዲሆንም የድርሻቸውን እየተወጡ መሆኑን ተናግረዋል።
በዓሉን ለማክበር ወደ ከተማው የሚመጡትን እንግዶች ተቀብለን ለማስተናገድ ዝግጅታችንን ጨርሰናል ሲሉም ገልጸዋል።