ምሁራን ችግር ፈቺ የጥናትና ምርምር ስራዎችን በማውጣት ለሀገር እድገት ያላቸውን ሚና ሊያጠናክሩ ይገባል-ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ - ኢዜአ አማርኛ
ምሁራን ችግር ፈቺ የጥናትና ምርምር ስራዎችን በማውጣት ለሀገር እድገት ያላቸውን ሚና ሊያጠናክሩ ይገባል-ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ
ሀዋሳ ፤መስከረም 19/2018 (ኢዜአ) :-ምሁራን ችግር ፈቺ የጥናትና ምርምር ስራዎችን በማውጣት ለሀገር እድገት ያላቸውን ሚና ሊያጠናክሩ እንደሚገባ የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ አሳሰቡ።
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናት ምርምር ተቋም ጋር በመተባበር ያዘጋጁት 22ኛው አለም አቀፍ የምርምር አውደ ጥናት በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ እየተካሄደ ነው።
በአውደ ጥናቱ መክፈቻ ላይ የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ እንዳሉት፤ የሀገርን ለውጥ ለማስቀጠልና የህብረተሰቡን ችግሮች በፍጥነትና በዘላቂነት ለመፍታት ምሁራን የምርምር ስራዎቻቸውን ሊያጠናክሩ ይገባል።
በተለይም ተቀዛቅዞ የቆየውን የምሁራን የሀገር ግንባታ ሚና ለማሳደግ የምርምር አውደ ጥናቶች ወጥና ተከታታይ በሆነ መልኩ መካሄድ አለባቸው ብለዋል።
በሀገር ላይ የሚሰነዘሩ አሉታዊ የማህበራዊ ሚዲያ ወሬዎችን በማጥራት ለሀገር ግንባታ መሰረት የሚጥሉ የፖሊሲ ግብዓትን በጥናት ማውጣት ላይም ምሁራኑ ይበልጥ እንዲሰሩም አሳስበዋል።
በየሶስት ዓመቱ የሚካሄዱ የምርምር አውደ ጥናቶች አሁን አለም እየሄደችበት ካለው ፍጥነት ጋር ኢትዮጵያን እኩል ማራመድ ባለመቻሉ የምርምር አውደ ጥናቶችን በየዓመቱ ማድረግ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ችሮታው አየለ (ዶ/ር) በበኩላቸው በዛሬው አለም አቀፍ የምርምር አውደ ጥናት ላይ የሚቀርቡ የምርምር ውጤቶች ለሀገር እድገት የፖሊሲ ግብዓትነት የሚያገለግሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።
አውደ ጥናቱ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ መካሄዱ ለዩኒቨርሲቲውና ለከተማዋ ትልቅ እድልን ይዞ እንደሚመጣም አስረድተዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ዳይሬክተር ዮሀንስ አድገ (ዶ/ር) በበኩላቸው አለም አቀፍ የምርምር አውደ ጥናቱ ከተመሰረተ 60 ዓመት እንዳስቆጠረና በተለያዩ ሀገራት ሲካሄድ እንደቆየ ተናግረዋል።
አውደ ጥናቱ በኢትዮጵያ በየሶስት ዓመቱ ሲካሄድ መቆየቱን ጠቁመው ለፖሊሲ አውጪዎችና ፈጻሚዎች በርካታ ጠቃሚ ግብዓት እንዳስገኘም አስረድተዋል።
አውደ ጥናቱ በሀገር ውስጥ መካሄዱ ለገጽታ ግንባታ፣ የፕሮጀክት ሀሳቦችን ለማንሸራሸር፣ የትብብር ፕሮጀክቶች ማዕቀፎችን ለመቅረጽና ለአዘጋጁ ዩኒቨርሲቲ በርካታ እድሎችን ይዞ እንደሚመጣም ጠቁመዋል።
አውደ ጥናቱ ለቀጣዮቹ አምስት ተከታታይ ቀናት የሚካሄድ ሲሆን በመድረኩም በርካታ የጥናትና ምርምር ስራዎች እንደሚቀርቡበትም ታውቋል።
በአውደ ጥናቱ ላይ የሲዳማ ክልል ምክትል ርዕስ መስተዳድርና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ በየነ በራሳ፣ የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ፣ የጀርመንና የፈረንሳይ ኤምባሲ ተወካዮች እንዲሁም በተለያዩ አህጉራት ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎችና የምርምር ተቋማት የተውጣጡ ተመራማሪዎች እየተሳተፉ ነው።