ቀጥታ፡

የሀገርን ሰላምና መረጋጋት በማጽናትና የሰላም እሴቶችን በመገንባት ለጋራ ልማትና ተጠቃሚነት መትጋት ይገባናል- የኃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች

ደሴ፤ መስከረም 19/2018(ኢዜአ)፡ የሀገርን ሰላምና መረጋጋት በማጽናትና የሰላም እሴቶችን በመገንባት ለጋራ ልማትና ተጠቃሚነት መትጋት ይገባናል ሲሉ የደሴ ከተማ የሐይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ተናገሩ።

የደሴ ከተማ አስተዳደር በወቅታዊ የፀጥታና ሰላም ጉዳዮች ዙሪያ ከሐይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት አካሂዷል።


 

የመድረኩ ተሳታፊዎችም የአካባቢን ብሎም የሀገርን ሰላምና መረጋጋት በማጽናትና የሰላም እሴቶችን በመገንባት ለጋራ ልማትና ተጠቃሚነት መትጋት ይገባናል ሲሉ ተናግረዋል። 

ከተሳታፊዎቹ መካከል ሊቀ መዘምራን አክሊሉ አረጋዊ፤ ከምንም ነገር በላይ ለሰላምና አብሮነታችን መስራትና በጋራ መቆም አለብን ብለዋል።

ከውጭና ከውስጥ የጥፋት ዓላማ በመሰነቅ ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር የሚሰሩ አካላት ድርጊታቸው በፍፁም ተቀባይነት የሌለው መሆኑን አንስተዋል።

የግጭትና ጦርነት ዓላማ ሰንቀው የሚሰራጩ የተሳሳቱና ሀሰተኛ መረጃዎችን በመተው መረጃን ከታማኝ ምንጮች በማጥራት እውነታን ማወቅ ተገቢ መሆኑንም መክረዋል። 

ሌላኛው የመድረኩ ተሳታፊ ሸህ አህመድ አረቡ፤ የህዝብን ሰላም በማናጋት በግርግር ጥቅማቸውን ለማካበት የሚንቀሳቀሱ አካላትን በጋራ መታገል ግድ መሆኑን አንስተዋል።

የደሴ ከተማ ህዝብ ምን ጊዜም ሰላምን በማጽናት መልማትና ሰርቶ መግባት የሚፈልግ መሆኑን ተናግረው አለመረጋጋት እንዲፈጠር የሚሰሩ አካላትን ፈፅሞ አይቀበልም ብለዋል። 

የአካባቢው የሀገር ሽማግሌ አቶ ጫኔ መንገሻ፤ በበኩላቸው የሰላምና የልማት ስራዎች ቀጣይነት ያለልዩነት በጋራ እንቆማለን፤ ለዚህም የደሴ ከተማና አካባቢው ህዝብ ዝግጁ ነው ሲሉ ተናግረዋል።


 

የደሴ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ፤  የተጀመሩ ልማቶችን ለማደናቀፍ የሚሰሩ የውስጥና የውጭ ተላላኪ ባንዳዎች  በጋራ መመከትና ሰላምን ማጽናት ከሁሉም እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።

በዚህ ረገድ የከተማ አስተዳደሩ ከህዝቡና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በልዩ ትኩረት የሚሰራ መሆኑንም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም