በምዕራብ ወለጋና አካባቢው የተፈጠረውን ሰላምና መረጋጋት ተከትሎ በሁሉም መስኮች የልማት ስራዎች በስፋት እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በምዕራብ ወለጋና አካባቢው የተፈጠረውን ሰላምና መረጋጋት ተከትሎ በሁሉም መስኮች የልማት ስራዎች በስፋት እየተከናወኑ ነው

ጊምቢ፤ መስከረም 19/2018 (ኢዜአ)፡-በምዕራብ ወለጋ ዞንና አካባቢው የተፈጠረውን ሰላምና መረጋጋት ተከትሎ በሁሉም መስኮች የልማት ስራዎች በስፋት እየተከናወኑ መሆኑን የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ።
በሀገር መከላከያ ሰራዊት ማእከላዊ ዕዝ የ103ኛ ጊቤ ኮር አራተኛ ዓመት የምስረታ በዓል በጊምቢ ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች እያከበረ ይገኛል።
የሰራዊቱ ከፍተኛ መኮንኖች፣ በዞኑ በየደረጃው የሚገኙ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች በተገኙበት መርሃ ግብሩ እየተካሄደ ነው።
በዚሁ ሁነት ላይ የተገኙት የምዕራብ ወለጋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ተሊላ ተረፈ፤ በዞኑ ቀደም ሲል የነበረው የጸጥታ ችግር በአካባቢው የልማትና ሌሎች እንቅስቃሴዎችም ላይ ተጽእኖ አሳድሮ እንደነበር አስታውሰዋል።
በዞኑ የተቀናጀ የጸጥታ ማስከበር ስራ በማከናወን በአካባቢው አስተማማኝ ሰላም መፈጠሩን አንስተው በዚህ ረገድ የመከላከያ ሰራዊት ላደረገው የላቀ አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል።
በምዕራብ ወለጋና አካባቢው የተፈጠረውን ሰላምና መረጋጋት ተከትሎ በሁሉም መስኮች የልማት ስራዎች በስፋት እየተከናወኑ መሆኑን አንስተው በተጠናከረ መልኩ የሚቀጥል መሆኑንም አረጋግጠዋል።
በዛሬው ቀን የ103ኛ ጊቤ ኮር አራተኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን ስናከብር በኮሩ የተገኙ ድሎችን በማስታወስ እና ላበረከቱት የላቀ አስተዋጽኦ ክብርና አድናቆት በመስጠት መሆኑን አንስተዋል።
በክብረ በዓሉ ላይ የተገኙ የሰራዊቱ አመራሮችና አባላትም ለሀገራቸው ክብርና ሉአላዊነት እንዲሁም ለህዝብ ደህንነት ስንል ማንኛውንም መስዋእትነት ለመክፈል ዝግጁ ነን ሲሉ አረጋግጠዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የማዕከላዊ ዕዝ አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ዘውዱ በላይ እና ሌሎች የሰራዊቱ አባላትና ከፍተኛ መኮንኖች አንዲሁም የቄለምና ምዕራብ ወለጋ ዞን አመራሮችና ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።