ቀጥታ፡

ፈረንሳይ ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሪፎርም ድጋፍ ማድረጓን ትቀጥላለች - አምባሳደር አሌክሲስ ላሜክ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 19/2018(ኢዜአ)፦ ፈረንሳይ ኢትዮጵያ እያከናወነች ለምትገኘው የኢኮኖሚ ሪፎርም ድጋፍ ማድረጓን እንደምትቀጥል በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር አሌክሲስ ላሜክ ገለጹ።

ኢትዮጵያ በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ፕሮግራም አማካኝነት የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሞች እያደረገች ትገኛለች።

የተለያዩ ዘርፎችን ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት የማድረግ፣ የፊስካል እና የሞኒተሪ ፖሊሲዎች ማሻሻያዎች፣ የእዳ አስተዳደር እና የንግድ ከባቢን ማሻሻል ከሪፎርሞቹ መካከል ይጠቀሳሉ።

በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር አሌክሲስ ላሜክ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ኢትዮጵያ እያሳየች ያለውን ከፍተኛ ለውጥ እና የሪፎርም ሂደት አድንቀዋል።

ፈረንሳይ ኢትዮጵያ እያደረገች ላለው የኢኮኖሚ ሪፎርም ድጋፍ በማድረጓ ኩራት እንደሚሰማትም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር እያከናወነች ላለው ስራ ፈረንሳይ ልምዷን ለማጋራት እንደምትሻ አምባሳደሩ ተናግረዋል።

ፈረንሳይ ከኢትዮጵያ ጋር በተለያዩ መስኮች ያላትን የሁለትዮሽ ትብብር ለማጠናከር ቁርጠኛ ናት ሲሉም ገልጸዋል።

ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ላላት የሁለትዮሽ ግንኙነት ትልቅ ቦታ እንደምትሰጥ ጠቁመው የኢትዮጵያ የቅርብ አጋር እና የኢትዮጵያውያን ወዳጅ ናት ሲሉም ተናግረዋል።

የፈረንሳይ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ድጋፍ እንደሚያደርጉም ነው ያስታወቁት።

ኢትዮጵያና ፈረንሳይ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የጀመሩት እ.አ.አ በ1897 መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም