ጊቤ ኮር ሰላም ከማረጋገጥ ባሻገር በልማትና በበጎ አድራጎት ስራዎች በመሳተፍ የህዝብ ልጅ መሆኑን በተግባር እያረጋገጠ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ጊቤ ኮር ሰላም ከማረጋገጥ ባሻገር በልማትና በበጎ አድራጎት ስራዎች በመሳተፍ የህዝብ ልጅ መሆኑን በተግባር እያረጋገጠ ነው
አዲስ አበባ፤ መስከረም 19/2018(ኢዜአ)፦ በማዕከላዊ ዕዝ 103ኛ ጊቤ ኮር የአካባቢውን ሰላም ከማረጋገጥ ባሻገር በልማትና በበጎ አድራጎት ስራዎች በመሳተፍ የህዝብ ልጅ መሆኑን በተግባር እያረጋገጠ ነው ሲሉ የ103ኛ ጊቤ ኮር አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል ጀማል ከድር ገለጹ፡፡
በማዕከላዊ ዕዝ ሥር የሚገኘው 103ኛ ጊቤ ኮር አራተኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን በምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች እያከበረ ይገኛል።
በበዓሉ ላይ የማዕከላዊ ዕዝ አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ዘውዱ በላይ፣ የምዕራብ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል መሰለ መሠረት፣ የሪፐብሊካን ኃይል አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ተስፋዬ ረጋሳ፣ የ103ኛ ጊቤ ኮር አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል ጀማል ከድር እና በርካታ የከተማዋ ነዋሪዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
የ103ኛ ጊቤ ኮር አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል ጀማል ከድር በበዓሉ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የጊቤ ኮር ባለፉት አራት ዓመታት አኩሪ ድል ማስመዝገቡን ተናግረዋል።
ጊቤ ኮር የተሰጠውን ግዳጅ በጀግንነት በመፈፀም የሀገርን ሰላምና ደህንነት እያረጋገጠ መሆኑን ተናግረው፤ የተሰማራባቸው የወለጋ ዞኖችን ከፀረ ሰላም ኃይሎች በማፅዳት አካባቢውን የልማት ቀጣና እያደረገ ይገኛል ብለዋል።
ኮሩ በአካባቢው ሰላም ከማረጋገጥ ባሻገር በልማትና በበጎ አድራጎት ስራዎች በመሳተፍ የህዝብ ልጅ መሆኑን በተግባር እያረጋገጠ መሆኑንም አብራርተዋል።
የምዕራብ ወለጋ ዞን አስተዳዳሪ ተሊላ ተረፋ በበኩላቸው፤ የ103ኛ ጊቤ ኮር ለዞኑ ሰላም መስፈንና ማህበራዊ ልማት ያበረከተው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው ብለዋል።
ኮሩ ለዞኑና ለአጎራባች ዞኖች ሰላምንና ደህንነትን ያረጋገጠ ጀግና ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ሰላም ከማረጋገጥ ባሻገር በተለያዩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች ላይ የጎላ ተሳትፎ እያደረገ እንዳለ ገልፀው፤ ሠራዊቱ ለህዝቡ ያለውን ፍቅር በልማት ስራዎችም አሳይቷል ነው ያሉት።