ቀጥታ፡

"ጋሪ ዎሮ" እሴቱ ተጠብቆ ለትውልድ እንዲተላለፍ የማስተዋወቅ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል 

አሶሳ፤ መስከረም 19/2018 (ኢዜአ)፦ የቦሮ ሽናሻ የዘመን መለወጫ በዓል "ጋሪ ዎሮ" እሴቱ ተጠብቆ ለትውልድ እንዲተላለፍ የማስተዋወቅ ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የብሔረሰቡ ተወላጆች ተናገሩ።

የቦሮ ሽናሻ ዘመን መለወጫ በዓል "ጋሪ - ዎሮ" በአሶሳ ከተማ ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰንን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች እና የብሔረሰቡ ተወላጆች በተገኙበት በፓናል ውይይት እና በአደባባይ ባህላዊ ክዋኔዎች ሲከበር ቆይቷል።

በበዓሉ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው ታዳሚዎች በዓሉ መከበሩ የብሔረሰቡን እሴቶች በማስተዋወቅ ለትውልድ እንዲተላለፍ ለማድረግ ያግዛል ብለዋል።

የበዓሉ ታዳሚ ከሆኑት መካከል ሞሲሳ ቢፍቱ እንደተናገሩት ጋሪ - ዎሮ በቀደምት የብሔረሰቡ ተወላጆች ሲከበር የቆየና በውስጡም አብሮነትንና ወንድማማችነትን የመሳሰሉ መልካም እሴቶችን የያዘ ነው።


 

በዓሉ ይቅር የሚባባሉበት፣ ቂምና ጥላቻ የሚወገዝበት እንዲሁም ተራርቀው የቆዩ ቤተሰቦች የሚገናኙበት በዓል መሆኑን ገልጸዋል።

ሌላኛዋ የበዓሉ ታዳሚ ወይዘሮ ሰዴቴ ወንበሮ በበኩላቸው የጋሪ - ዎሮ በዓል በድምቀት እንዲከበር የብሔረሰቡ መገለጫ የሆኑ የምግብ እና የመጠጥ ዓይነቶችን በማዘጋጀት ለታዳሚው እንዳቀረቡ ተናግረዋል።


 

በዓሉ በተለይም ወጣቶች የትዳር አጋራቸውን የሚያገኙበት ባህል እና እሴቱን የሚማሩበት ልዩ ቀን መሆኑን ጠቁመዋል።

የጋሪ - ዎሮ በዓል በአዲስ አበባ እና በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች መከበሩ የብሔረሰቡን እሴቶች ከማስተዋወቅ ባለፈ የህዝቦችን ትስስር ያጠናክራል ያለችው ደግሞ "ሚስ ጋሪ-ዎሮ 2018" ሆና የተመረጠችው ወጣት ምንታምር ሞርካ ነች።


 

በዓሉ የልጃገረዶች ውበት የሚገለጥበት እና በባህላዊ አልባሳት የሚያጌጡበት መሆኑን ገልፃ ከትልልቅ አባቶች ጋር በመሆን የብሔረሰቡ ማንነት እና እሴቶች እንዲተዋወቁ ለማድረግ ኃላፊነቴን እወጣለሁ ብላለች።

የቦሮ ሽናሻ ብሔረሰብ ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ አቶ ሀብታሙ አርገታ በበኩላቸው፤ የዘንድሮው በዓል የዓመታት ጥያቄ የነበረው የጋሪ - ዎሮ ማክበሪያ ቦታ ምላሽ ያገኘበት በመሆኑ የተለየ ያደርገዋል ብለዋል።


 

የቦሮ ሽናሻ ብሔረሰብ ከሌሎች ጋር በፍቅር እና በአንድነት የሚኖር የቱባ ባህል እና እሴት ባለቤት መሆኑንም ገልጸዋል።

ጋሪ-ዎሮ በብሔረሰቡ ዘንድ አዲስ ዘመን መምጣቱን፣ ጨለማ ማለፉን፤ ችግር መወገዱን የሚያበስር በዓል ሲሆን፣ ለሚቀበሉት አዲስ ዓመት ደግሞ ተስፋን፣ አንድነትን፣ መቻቻልንና ፍቅርን የሚያበስር መሆኑ ተመላክቷል፡፡ 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም