ቀጥታ፡

ለኢትዮጵያ አዳጊዎችና ወጣቶች የኪነ ጥበብ ፈጠራና ለባህል ዕድገት ምቹ ማዕከላትን እየገነባን ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 18/2018(ኢዜአ)፦ ለኢትዮጵያ አዳጊዎችና ወጣቶች የኪነ ጥበብ ፈጠራና ለባህል ዕድገት ምቹ ማዕከላትን እየገነባን ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ዛሬ ዘመኑን በዋጀ መልኩ የተገነባውን የአዲስ አበባ ሕጻናት እና ወጣቶች ቴአትር እና ሲኒማ ኮምፕሌክስን መርቀን ለአገልግሎት ከፍተናል ብለዋል።


 

የመጪው ዘመን የኢትዮጵያ የኪነ ጥበብ ፈርጦች የሚፈልቁበት ይህ ማዕከል በትውልድና በሀገር ግንባታችን የኪነ ጥበብን ጉልበት ለመጠቀም መንግሥት የሰጠውን ትኩረት ያሳያል ሲሉም ገልጸዋል።

አዲስ አበባ በፈጣን የከተማ ልማት ጉዞዎቿ ለኪነ ጥበብና ለብዙ አንጋፋ ከያንያን ከፍተኛ የሆነ መደላድል የፈጠረች ከተማ መሆኗን በተግባር እያሳየች ትገኛለች ነው ያሉት።

ዛሬ ያስመረቅነው ማዕከልም የጥበብ ፈጠራ ከባህል ጋር የሚገናኝበት፣ የአዳጊዎች ሕልም የሚጎለብትበት፣ የኢትዮጵያ ወጣቶች በቴአትርና በሲኒማ ጎልተው የሚወጡበት የልህቀት ሥፍራ ሆኖ ያገለግላል ሲሉ ገልጸዋል።


 

ከያንያንም የሀገራችሁንና የመዲናችሁን ገጽታ እንድታጎሉና እንድታስተዋውቁ፣ አብሮነት እንድታጠናክሩና ትውልዱን እንድታንፁ አደራ ማለት እፈልጋለሁ ብለዋል።

ለገናናዋ ኢትዮጵያ ማንሠራራት በባህል፣ በፈጠራ እና በብሔራዊ ኩራትና ትርክት ግንባታ ላይ የጀመርነውን ሥራ አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም