በማዕከላዊ ዕዝ ሥር የሚገኘው 103ኛ ጊቤ ኮር ትውልድ ተሻጋሪ ገድል የፈፀመ ነው - ሜጀር ጄኔራል ተስፋዬ ረጋሳ - ኢዜአ አማርኛ
በማዕከላዊ ዕዝ ሥር የሚገኘው 103ኛ ጊቤ ኮር ትውልድ ተሻጋሪ ገድል የፈፀመ ነው - ሜጀር ጄኔራል ተስፋዬ ረጋሳ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 18/2018(ኢዜአ)፦ በማዕከላዊ ዕዝ ሥር የሚገኘው 103ኛ ጊቤ ኮር ትውልድ ተሻጋሪ ገድል የፈፀመ ነው ሲሉ የሪፐብሊካን ጥበቃ ኃይል አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ተስፋዬ ረጋሳ ገለጹ፡፡
በማዕከላዊ ዕዝ ሥር የሚገኘው 103ኛ ጊቤ ኮር አራተኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን በምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ከተማ ማክበር ጀምሯል፡፡
ጊቤ ኮር ከተመሰረተ ጀምሮ ባለፉት አራት ዓመታት ያከናወነውን የግዳጅ አፈጻጸም በሚያሳይ የፓናል ውይይትና የፎቶ አውደ ርዕይ እያከበረ ይገኛል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የማዕከላዊ ዕዝ አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ዘውዱ በላይ፣ የሪፐብሊካን ኃይል አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ተስፋዬ ረጋሳ፣ የ103ኛ ጊቤ ኮር አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል ጀማል ከድር፣ የአካባቢው ነዋሪዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
የሪፐብሊካን ጥበቃ ኃይል አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ተስፋዬ ረጋሳ የኮሩን አመሰራረት በተመለከተ በፓናል ውይይቱ ላይ እንደተናገሩት፤ ኮሩ በአጭር ጊዜ ውስጥ ራሱን ችሎ በመቆም ለተቋሙ አለኝታ መሆኑን አስታውቀዋል።
ኮሩ በውጫሌ፣ በአምባሰል፣ በጊራና፣ በቢስቲማ፣ በከሚሴ፣ በአጣዬ፣ በጃዋ፣ በሺናባና በጋሸና እንዲሁም በሰቆጣ ግንባሮች ተዋግቶ ያስመዘገባቸው ውጤቶች ታላቅ መሆናቸውን ጠላት የማይክደው እውነታ ነው ብለዋል።
በርካታ እልህ አስጨራሽ ውጊያዎችን በማድረግ አንፀባራቂ ድሎችን ያስመዘገበው ኮሩ፤ ትውልድ ተሻጋሪ ገድል የፈፀመ ነው ሲሉ ገልፀዋል።
103ኛ ጊቤ ኮር ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ ብዙ ጀግኖችን በማፍራት የሀገርን ሰላም በማስጠበቅ ላከናወነው ተግባር ክብርና ምስጋና ይገባዋል ብለዋል።