ጊቤ ኮር በአካባቢው ሰላም በማስፈን ነዋሪዎች የልማት ስራዎችን በተረጋጋ መልኩ እንዲያከናውኑ እያደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ጊቤ ኮር በአካባቢው ሰላም በማስፈን ነዋሪዎች የልማት ስራዎችን በተረጋጋ መልኩ እንዲያከናውኑ እያደረገ ነው

አዲስ አበባ፤ መስከረም 18/2018(ኢዜአ)፦ በማዕከላዊ ዕዝ ሥር የሚገኘው 103ኛ ጊቤ ኮር በአካባቢው ሰላም በማስፈን ነዋሪዎች የልማት ስራዎችን በተረጋጋ መልኩ እንዲያከናውኑ እያደረገ መሆኑን የማዕከላዊ ዕዝ አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ዘውዱ በላይ ገለጹ።
በማዕከላዊ ዕዝ ሥር የሚገኘው 103ኛ ጊቤ ኮር አራተኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን በምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ከተማ ማክበር ጀምሯል፡፡
ጊቤ ኮር ከተመሰረተ ጀምሮ ባለፉት አራት ዓመታት ያከናወነውን የግዳጅ አፈጻጸም በሚያሳይ የፓናል ውይይትና የፎቶ አውደ ርዕይ ማክበር ጀምሯል።
በበዓሉ ላይ የማዕከላዊ ዕዝ አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ዘውዱ በላይ፣ የሪፐብሊካን ኃይል አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ተስፋዬ ረጋሳ፣ የ103ኛ ጊቤ ኮር አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል ጀማል ከድር፣ የአካባቢው ነዋሪዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
በፓናል ውይይቱ ወቅት የማዕከላዊ ዕዝ አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ዘውዱ በላይ እንደገለጹት፤ የ103ኛ ጊቤ ኮር ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ በተሰማራበት ቀጣና ግዳጁን በብቃት እየተወጣ ይገኛል።
ኮሩ በተሰማራበት አካባቢ ሠላምና ደህንነትን በማረጋገጥ ረገድ እየፈፀመ ያለው ገድል አበረታች መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም የአካባቢው ነዋሪዎች የዕለት ተዕለት ሥራቸውን ተረጋግተው እንዲያከናውኑ ማስቻሉን ጠቅሰዋል።
ኮሩም በተሰማራበት የግዳጅ ቀጣና ተልዕኮ የመፈፀም ብቃቱን አጠናክሮ በመቀጠል ራሱን ለትልቅ ሀገራዊ ግዳጅ ማዘጋጀት እንዳለበት አስገንዘበዋል።
የፓናል ውይይቱን በንግግር የከፈቱት የ103ኛ ጊቤ ኮር ምክትል አዛዥ ኮሎኔል አያነው አበበ በበኩላቸው፤ ኮሩ በተሰማራበት የግዳጅ ቀጣና የጠላትን እንቅስቃሴ በመከታተል በሸኔ ታጣቂ ላይ ሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራ ማድረሱን ገልጸዋል።
አክለውም ኮሩ ሀገራዊ ተልዕኮዎችን በብቃት ከመወጣቱ በተጨማሪ የሕዝብን ደህንነትና ሠላም በማረጋገጥ ሕዝብና መንግሥት የሰጡትን አደራ እየተወጣ ይገኛል ብለዋል።
በተለይም ኮሩ በአካባቢው ሰላምን በማስጠበቅ፣ የሕግ የበላይነትን በማስፈንና የልማት ስራዎች እንዲከናወኑ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
የኮሩ አራተኛ ዓመት የምስረታ በዓል ሠራዊቱ እንደ ሀገር የተወጣውን እና እየተወጣ ያለውን ግዳጅ በሚያሳዩ መርኃ ግብሮች መከበር ጀምሯል።