የተጀመረውን ሀገራዊ የብልጽግና ጉዞ ለማፋጠን ዲጂታል አሰራርን ማጠናከር ይገባል - ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የተጀመረውን ሀገራዊ የብልጽግና ጉዞ ለማፋጠን ዲጂታል አሰራርን ማጠናከር ይገባል - ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር)

ባህር ዳር፤ መስከረም 18/2018(ኢዜአ)፡- ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመገንባት የተጀመረውን ሀገራዊ የብልጽግና ጉዞ ለማፋጠን ዲጂታል አሰራርን ማጠናከር እንደሚገባ የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር) ገለጹ።
"ጠንካራ የመንግስት ኢንቨስትመንት ሥርዓትና የመረጃ ጥራት ለዘላቂ ልማት" በሚል መሪ ሃሳብ የውይይት መድረክ በባህርዳር ተካሂዷል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር) እንደገለጹት እንደሀገር ልማትን በማጠናከር ድህነትን ታሪክ ለማድረግና ሀገራዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቷል፡፡
ጠንካራ ኢኮኖሚን ለመገንባትና ኢንቨትስትመንትን ለማስፋፋት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፣ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴን በማጠናከር የተጀመረውን ሀገራዊ ብልጽግና ለማፋጠን ዲጂታል አሰራርን መከተል ይገባል ብለዋል።
ለዚህም ጠንካራ የመንግስት የኢንቨስትመንት ስርዓትና የመረጃ ጥራት ግንባታ ላይ በትኩረት መስራትና ሁለንተናዊ የልማት ሥራውን በዲጂታል አሰራር ማገዝ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በተጨማሪም የስታትስቲክስ ልማት ፕሮግራም፣ የመንግስት ኢንቨስትመንት ማኔጅመንት እና ዲጂታል ፕላኒንግና የሪፖርት ስርዓትን መተግበር ይገባል ሲሉም ገልጸዋል።
በክልሉ በሚገኙ የመንግስት ተቋማት የሚከናወኑ የልማትና የኢንቨስትመንት ሥራዎችን ከፌደራል ጋር የተጣጣሙ ከማድረግ ባለፈ የተናበበ የትግበራ አቅጣጫ እንዲከተሉ በትኩረት መስራት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ የክልሉ መንግስት በፕሮጀክት አፈጻጸም ላይ መሻሻል ከማሳየት ባለፈ ዲጂታል ትግበራን ጨምሮ ሌሎች የእድገት መሰረት የሆኑ አሰራሮችን አስቀድሞ ተግባራዊ አድርጓል ብለዋል።
አሰራሮቹ በክልሉ ይስተዋሉ የነበሩ ችግሮችን ከመፍታት ጎን ለጎን ዘላቂ የኢኮኖሚ እድገትን በማረጋገጥ የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ያለሙ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ሚኒስቴሩ በኢንቨስትመንት፣ በዲጂታል፣ በዕቅድና በሪፖርት አቀራርብ ላይ ያመጣቸውን አዳዲስ አሰራሮች በትክክል መተግበር ከተቻለ በሀገር ደረጃ ወጥ አተገባበር እንዲኖር ያስችላል ነው ያሉት።
በተለይም የሚመዘገበውን ኢኮኖሚያዊ እድገትና የፕሮጀክት አፈጻጸም በዲጂታል የመለካት አሰራር ሳይንሳዊ የመረጃ አቅርቦትን እውን ስለሚያደርግ ፈጥኖ መተግበር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በመድረኩ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።