በክልሉ የትምህርት ጥራት ለማረጋገጥና ተደራሽነትን ለማስፋት ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ የሚከናወነው ተግባር ተጠናክሮ ቀጥሏል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የትምህርት ጥራት ለማረጋገጥና ተደራሽነትን ለማስፋት ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ የሚከናወነው ተግባር ተጠናክሮ ቀጥሏል
ሮቤ፤ መስከረም 18/2018(ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን ለማስፋት ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ የሚከናወነው ተግባር ተጠናክሮ መቀጠሉን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።
የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ቶላ በሪሶ(ዶ/ር) እና ሌሎች የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በባሌ ዞን በርበሬ ወረዳ ከ48 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የተገነባውን የጬከታ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መርቀው አገልግሎት አስጀምረዋል።
ትምህርት ቤቱ የተገነባው ''ኢማጅን ዋን ዴይ" በተባለ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅትና ህብረተሰቡ ባደረገው ተሳትፎ መሆኑ ተመልክቷል።
የቢሮው ኃላፊ ቶላ በሪሶ(ዶ/ር) በወቅቱ እንዳሉት በክልሉ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥና ተደራሽነትን ለማስፋት ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ እየተሰራ ያለው ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል።
የክልሉ መንግሥት ባለፉት ዓመታት ባደረገው ጥረት፣ በአጋር አካላት ድጋፍና በማህበረሰቡ ተሳትፎ በተሰሩት ሥራዎች የትምህርት ተደራሽነት መሻሻል መቻሉን አስታውሰዋል።
በባሌ ዞን በርበሬ ወረዳ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ባልተዳረሰባቸው አርብቶ አደር ወረዳዎች አካባቢ በኢማጅን ዋን ዴይና በህብረተሰቡ ተሳትፎ ተገንብቶ ለአገልግሎት የበቃው ትምህርት ቤት የጥረቱ ማሳያ ነው ብለዋል።
ትምህርት ቤት መገንባት ብቻውን ግብ አይደለም ያሉት ሃላፊው፤ ህብረተሰቡ ልጆቹን ወደ ትምህርት ቤት በመላክ የተሻለ ትምህርት እንዲያገኙ እንዲያደርግም ጠይቀዋል።
በቀጣይም ቢሮው በክልሉ ትምህርት ቤቶች ባልተዳረሰባቸው ገጠራማ አካባቢዎች የማስፋት ሥራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
በ2017 የትምህርት ዘመን የሀገር አቀፍ ፈተና በሀገር ደረጃ የተመዘገበው ከፍተኛ ውጤት በተማሪዎች መካከል መነሳሳትን የፈጠረና የትምህርት ቤት ደረጃዎች ከተሻሻሉ የሚታሰበውን ግብ ማሳካት እንደሚቻል ትልቅ ማሳያ እንደሆነ አመልክተዋል።
የባሌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አብዱልሀኪም አልይ በበኩላቸው ትምህርት ቤቱ የተገነባው የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ባልተዳረሰበት የዞኑ አርብቶ አደር ማህበረሰብ አካባቢ መሆኑ ልዩ እንደሚያደርገው ተናግረዋል።
ትምህርት ቤቱ ስምንት የመማሪያ ክፍሎች፣ ቤተ መጻሕፍት፣ የመምህራንና የአስተዳደር ቢሮዎች እንዲሁም የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን ያካተተ እንደሆነም ገልጸዋል።
በድርጅቱ ድጋፍ የተገነባው ትምህርት ቤት መንግስት ትምህርትን ለዜጎች ለማዳረስ እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ የሚያግዝ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የ"ኢማጅን ዋን ዴይ" ድርጅት የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ሰኢድ አማን(ዶ/ር) ናቸው።
በዚህም በርበሬ ወረዳ ህብረተሰቡን በማሳተፍ ጭምር ከ48 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመገንባት ለአገልግሎት ማብቃታቸውን አስታውቀዋል።
የአካባቢው ነዋሪዎች በበኩላቸው ትምህርት ቤቱ በአካባቢያቸው መገንባቱ ልጆቻቸው ሳይርቁ የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ የሚያስችል በመሆኑ ተሳታፊ ባለድርሻ አካላትን አመስግነዋል።