ቀጥታ፡

የጎንደር አብያተ መንግስት ኪነ ህንጻዎችን የሚጎበኙ ቱሪስቶችን ቆይታ ማራዘም የሚያስችል ፕሮጀክት ተቀርፆ ወደ ተግባር ተገብቷል

ጎንደር፤ መስከረም 18/2018(ኢዜአ)፡- የጎንደር አብያተ መንግስት ኪነ ህንጻዎችን የሚጎበኙ ቱሪስቶችን ቆይታ ማራዘም እንዲቻል ፕሮጀክት ተቀርፆ ተግባራዊ እንቅስቃሴ መጀመሩን የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ አስታወቁ።

በአብያተ መንግስቱ የነገስታቶችን ህይወት የሚገልጹ ታሪካዊ ትእይንቶች የቀረቡበትን ፕሮጀክት ሚኒስትሯ በይፋ አስጀምረዋል፡፡


 

በፕሮጀክቱ ማስጀመሪያ ስነ ስርአት ላይ ሚኒስተሯ እንደተናገሩት መንግስት በሀገሪቱ የሚገኙ ዋና ዋና የቱሪስት መዳረሻዎችን በማደስ፣ በመንከባከብና በመጠበቅ ረገድ ውጤታማ ተግባራት አከናውኗል፡፡

የአጼ ፋሲል አብያተ መንግስትን ጨምሮ ነባርና ጥንታዊ ቅርሶችን ታሪካዊ ገጽታቸውን በጠበቀ መንገድ እድሳትና ጥገና ተደርጎላቸው ለመጪው ትውልድ ታሪካቸው ተጠብቆ እንዲቆይ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል፡፡

ህይወት በአብያተ መንግስት በሚል በአጼ ፋሲል አብያተ መንግስት በይፋ የተጀመረው ፕሮጀክት የቀደምት ነገስታቱን ታሪክ በተለያዩ ትእይንቶች ለቱሪስቶች የሚቀርብበት የሙከራ ፕሮጀክት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ፕሮጀክቱ በ17ኛው ክፍለ ዘመን የነገስታቱን የአኗኗር ዘይቤ፣ የስርአተ መንግስታቸውን የአመራር ጥበብ፣ የሀገር ፍቅርና ሌሎች ታሪካዊ ትእይንቶችን አሁን ላለው ትውልድ በማሳየት ህያው ታሪክን ጠብቆ የማስቀጠል አላማ ያለው ነው ብለዋል፡፡

ፕሮጀክቱን በታሪክ ተመራማሪዎች፣ አጥኚዎችና አዋቂዎች እንዲሁም በጥበብ ሰዎች በየጊዜው በሃሳብ እንዲዳብር በማድረግ አብያተ መንግስቱን የሚጎበኙ ቱሪስቶችን ቆይታ ለማራዘም ምቹ ስነ ምህዳር ለመፍጠር መታሰቡን አውስተዋል፡፡


 

የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ መልካሙ ጸጋዬ በበኩላቸው በአጼ ፋሲል አብያተ መንግስት የተጀመረው ፕሮጀክት ከዚህ ቀደም ኪነ ህንጻዎችን ብቻ የሚጎበኙ ቱሪስቶች የነገስታቱን ህያው ታሪክ በትእይንት መልክ ጭምር እንዲጎበኙ የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡

የፕሮጀክቱ መጀመር የቱሪስቶችን ቆይታ በማራዘምና ፍሰቱን በመጨመር ከቱሪዝም የሚገኘውን ገቢ በማሳደግ የአካባቢውን ህብረተሰብ ተጠቃሚ በማድረግ በኩል ትልቅ ተስፋ የተጣለበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ኢኒሼቲቭ የእድሳትና የጥገና ስራው እየተከናወነ የሚገኘው የአጼ ፋሲል አብያተ መንግስት ዓለም አቀፍ ቅርስ ጎንደርን ተመራጭ የቱሪስት መዳረሻ በማድረግ በኩል የጎላ ፋይዳ አምጥቷል ያሉት ደግሞ የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው ናቸው፡፡

ህይወት በአብያተ መንግስት በሚል በፌደራልና በክልሉ መንግስት በይፋ የተጀመረው ፕሮጀክት የከተማውን ቱሪዝም የሚያነቃቃ በመሆኑ የከተማ አስተዳደሩ ድጋፍና ክትትል እንደማይለየው አረጋግጠዋል፡፡


 

በፕሮጀክቱ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ የፌደራልና የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ጥሪ የተደረገላቸው አርቲስቶችና ታሪክ አጥኚዎች የተገኙ ሲሆን የቤተ መንግስቱን የነገስታት የቀደመ ህይወት የሚያስቃኙ ትእይንቶችም ለእይታ ቀርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም