ቀጥታ፡

ለተቀላጠፈ አገልግሎት አሰጣጥ ተደራሽነት ዘመኑን የሚመጥንና በቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራር መዘርጋት ወቅቱ የሚጠይቀው ጉዳይ ነው - ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ

ባህር ዳር፤ መስከረም 18/2018(ኢዜአ)፦ ለቀልጣፋ አገልግሎት አሰጣጥ ተደራሽነት ዘመኑን የሚመጥንና በቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራር መዘርጋት አስፈላጊና ወቅቱ የሚጠይቀው ጉዳይ ነው ሲሉ ‎‎የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ።

የአማራ ክልል መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ክልላዊ የሥራ ማስጀመሪያ መርሃ-ግብር ዛሬ በባህር ዳር ከተማ ተካሂዷል።

‎‎ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ በምረቃው ላይ እንዳሉት መንግስት ቀልጣፋ የአገልግሎት አሰጣጥን ተደራሽ ለማድረግ ዘርፈ ብዙ ጥረቶች እያደረገ ይገኛል።


 

ቀልጣፋ የአገልግሎት አሰጣጥ ተደራሽ ለማድረግም ዘመኑን የሚመጥንና በቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራር መዘርጋት አስፈላጊና ወቅቱ የሚያስገድድ ጉዳይ ነው ብለዋል።

‎በፌዴራል ደረጃ የተጀመረው ዘመኑን የዋጀ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ማዕከል ወደ ክልሉ እንዲመጣ ጥረት ሲደረግ መቆየቱንም አስታውሰዋል።

‎የክልሉ መንግስት ማዕከሉ በፍጥነት እንዲጠናቀቅ በማድረጉ በክልል ደረጃ በዛሬው ዕለት ስራ እንዲጀመር መደረጉንም ተናግረዋል።

‎ይህም ጊዜና ጉልበትን በመቆጠብ እንዲሁም ፍትሃዊነትንና ተጠያቂነትን በማስፈን የንግድና ኢንቨስትመንት ስርዓቱ በአግባቡ እንዲሳለጥ ያደርጋል ብለዋል።


 

‎የአማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስና ሰው ሃብት ልማት ቢሮ ሃላፊ ባንችአምላክ ገብረማሪያም በበኩላቸው ዛሬ ተመርቆ ሥራ የጀመረው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት አስር የክልልና አራት የፌዴራል ተቋማት ተለይተው ወደ ሲስተም እንዲገቡ የተደረገበት ነው ብለዋል።

‎ከክልሉ በተጨማሪ ባህር ዳር፣ ጎንደር እና ደሴ ሪጂኦ ፓሊታንት ከተሞችን መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ስርዓት ለማስጀመር ስራዎች እየተፋጠኑ መሆኑን ጠቁመው፣ በሌሎች ከተሞችም እንደሚስፋፋ ገልጸዋል።

በመርሃ-ግብሩ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር) እና ሌሎች የክልልና የፌዴራል የመንግስት የሥራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።‎

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም