ቀጥታ፡

የመንግስት ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥን ዘመናዊ፣ ፈጣንና ቀልጣፋ የሚያደርጉ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ ነው - ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር)

ባህርዳር፤ መስከረም 18/2018(ኢዜአ)፦ የመንግስት ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥን ዘመናዊ፣ ፈጣንና ቀልጣፋ የሚያደርጉ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር) ተናገሩ።

በአማራ ክልል ባሕር ዳር ከተማ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ፣ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር) እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች መርቀው ስራ አስጀምረዋል።


 

በዚሁ መርሃ ግብር ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር)፣ እንደ ሀገር የአገልግሎት አሰጣጥ ችግርን በዘላቂነት በመፍታት ቀልጣፋ አሰራር ለመዘርጋት የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል።

ለዚህም አንዱ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መሆኑን አንስተው በሁሉም አካባቢዎች ተግባራዊ እየተደረገ ነው ብለዋል።


 

የመንግስት ተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥን ዘመናዊ፣ ፈጣንና ቀልጣፋ ማድረግ የሚያስችሉ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን አንስተው በተጠናከረ መልኩ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

በሁሉም ዘርፎች የተጀመሩ የሪፎርም ስራዎች ተጨባጭ ውጤቶች እያመጡ መሆኑን አንስተው መሰል ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም