ኢሬቻን ባህላዊ ትውፊቱን በጠበቀ መልኩ በልዩ ድምቀት ለማክበር ተዘጋጅተናል - አባ ገዳዎች - ኢዜአ አማርኛ
ኢሬቻን ባህላዊ ትውፊቱን በጠበቀ መልኩ በልዩ ድምቀት ለማክበር ተዘጋጅተናል - አባ ገዳዎች
አዲስ አበባ፤ መስከረም 18/2018(ኢዜአ)፦ የዘንድሮውን ኢሬቻ ባህላዊ ትውፊቱን በጠበቀ መልኩ በልዩ ድምቀት ለማክበር ተዘጋጅተናል ሲሉ አባ ገዳዎች ገለጹ።
ኢዜአ ያነጋገራቸው አባገዳዎች ኢሬቻ የኦሮሞ ሕዝብ ለፈጣሪ ምስጋና ከሚያቀርብባቸው ቱባ ባህሎች መካከል አንዱ መሆኑን ገልጸዋል።
አባገዳ ግርማ በቀለ ኢሬቻ አስቸጋሪ የነበረው የክረምት ወቅት አልፎ ወደ ብራ መሸጋገራችንን የምናበስርበት ነው ብለዋል።
በክረምት ወቅት በነበረው ዝናብ የወንዝ ሙላትና ጎርፍ በመሳሰሉ ምክንያቶች የተራራቁ ቤተዘመዶችና ህዝቡ የወንዝ ሙላቱ ቀንሶና ብርሃን ፈንጥቆ ዳግም የሚገናኙበት፣ የሚጠያየቁበትና ለፈጣሪ ምስጋና የሚያቀርቡበት መሆኑንም ገልጸዋል።
የኢሬቻ በዓል በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት(ዩኔስኮ) የዓለም ቅርስ ሆኖ የተመዘገበው የገዳ ሥርዓት አንዱ መገለጫ መሆኑን ጠቅሰው፥ ኢሬቻም ለብቻው እንዲመዘገብ የሚመለከተው አካል ሊሰራ ይገባል ነው ያሉት።
ኢሬቻ ሁሉም በጋራ የሚያከበረውና የአብሮነት መገለጫ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ አባገዳ ወልደ አብ ናቸው።
በዓሉ የምስጋና፣ የሰላምና የአንድነት በዓል መሆኑን ጠቅሰው፥ ለህዝቦች መስተጋብር አስተዋጽኦ ያለው መሆኑን ገልጸዋል።
ዘንድሮ የሚከበረው ኢሬቻ ሀገራችን ታላቁ የሕዳሴ ግድብን ባስመረቀችበት ማግስት እንዲሁም በኮሪደር ልማት ሰፋፊ ስራዎች በተሰሩት ወቅት መሆኑ ልዩ ያደርገዋል ሲሉ አባገዳዎቹ ተናግረዋል።
በዓሉ ባህላዊ ትውፊቱን በጠበቀ መልኩ እንዲከበር ዝግጅት በማድረግ ላይ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው ኢሬቻን ጨምሮ በኢትዮጵያ የሚከበሩ የአደባባይ በዓላት ሰላምን፣ ፍቅርንና አንድነትን የሚያጠናክሩ ናቸው ብለዋል።
ኢሬቻ የኦሮሞ ህዝብ ለረጅም ዓመታት ጠብቆ ካቆያቸው ድንቅ የገዳ ማህበራዊ እሴቶች መካከል አንዱ መሆኑን በማንሳት፥ የፍቅርና የአብሮነት መገለጫ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢሬቻ ለቱሪዝም መስህብነት ብሎም ለሀገር ኢኮኖሚ እድገት ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለውም ተናግረዋል።
ባህላዊ አሴቱን ጠብቆ ከትወልድ ወደ ትውልድ እንዲሸጋገር ማልማትና መንከባከብ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።