ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በሴቶች ከ20 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ የማጣሪያ የመልስ ጨዋታዋን ከኬንያ ጋር ታደርጋለች

አዲስ አበባ፤ መስከረም 18/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ሴቶች ብሄራዊ ቡድን የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የመልስ ጨዋታውን ዛሬ ከኬንያ አቻው ጋር ያደርጋል።

የሁለቱ ሀገራት ጨዋታ ከቀኑ 9 ሰዓት ኖይሮቢ በሚገኘው ኡሊንዚ ስፖርት ኮምፕሌክስ ይካሄዳል። 

ሀገራቱ በአበበ በቂላ ስታዲየም ከሳምንት በፊት ባደረጉት ጨዋታ አንድ አቻ ተለያይተዋል።

በቻለው ለሜቻ የሚመራው ቡድን ከመጀመሪያው ጨዋታ በኋላ በአዲስ አበባ ዝግጅቱን ሲያደርግ ቆይቶ ከትናንት በስቲያ ወደ ናይሮቢ ማቅናቱ የሚታወስ ነው።

ቡድኑ ከጨዋታው በፊት የመጨረሻ  ልምምዱን በኡሊንዚ ስፖርት ኮምፕሌዝ ትናንት ማድረጉን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል። 

በጃክሊን ጁማ የሚመራው የኬንያ ከ20 ዓመት በታች ሴቶች ብሄራዊ ቡድን ከመጀመሪያው ጨዋታ መልስ በናይሮቢ ዝግጅቱን ሲያደርግ ቆይቷል። 

ኢትዮጵያ በደርሶ መልስ ውጤት ካሸነፈች በሶስተኛው ዙር ከታንዛንያና አንጎላ አሸናፊ ጋር ትጫወታለች።

በፖላንድ አስተናጋጅነት እ.አ.አ በ2026 ለሚካሄደው 12ኛው የሴቶች ከ20 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ 24 ሀገራት ይሳተፋሉ።

አፍሪካ በውድድሩ ላይ አራት ሀገራት የማሳተፍ ኮታ ያገኘች ሲሆን ሀገራት በአራት ዙር የማጣሪያ ጨዋታቸውን እንደሚያደርጉ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም