ኒውካስትል ዩናይትድ ከአርሰናል የሚደረገው የዛሬው ጨዋታ ተጠባቂ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኒውካስትል ዩናይትድ ከአርሰናል የሚደረገው የዛሬው ጨዋታ ተጠባቂ ነው

አዲስ አበባ፣ መስከረም 18/2018(ኢዜአ)፡- በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የ6ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ዛሬ ኒውካስትል ዩናይትድ ከአርሰናል የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል።
የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ 52ሺህ ተመልካች በሚያስተናግደው ሴንት ጀምስ ፓርክ ስታዲየም ምሽት 12 ሰዓት ከ30 ላይ ይካሄዳል።
ኒውካስትል ዩናይትድ በስድስት ነጥብ 15ኛ ደረጃን ሲይዝ አርሰናል በ10 ነጥብ ሰባተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ቡድኖቹ ቀደም ሲል በሁሉም ውድድሮች በ197 ጨዋታዎች ተገናኝተው አርሰናል 86ቱን በማሸነፍ የበላይነቱን ሲይዝ ኒውካስትል ዩናይትድ 72 ጊዜ ድል ሲቀናው 39 ጊዜ አቻ ተለያይተዋል።
ሁለቱ ክለቦች ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኙት እ.አ.አ 1893 ሲሆን በሁለተኛ ዲቪዚዮን ባደረጉት ጨዋታ ሁለት አቻ ተለያይተዋል።
ሁለቱ ቡድኖች በተገናኙባቸው ባለፉት አምስት የሊጉ ጨዋታዎች አርሰናል ሶስት ጊዜ ሲያሸንፍ ኒውካስትል ዩናይትድ ሁለቱን አሸንፏል።
በሊጉ ጥሩ ጅማሮ ያላሳየው ኒውካስትል ዩናይትድ የዛሬውን ጨዋታ ካሸነፈ በደረጃ ሰንጠረዡ ከወገብ በላይ ከፍ የሚልበትን እድል ያገኛል።
አርሰናል ካሸነፈ ደግሞ ከሊጉ መሪ ሊቨርፑል ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ ሁለት ዝቅ ያደርጋል።
የ38 ዓመቱ አውስትራሊያዊ ጃሬድ ጂሌት ጨዋታውን በዋና ዳኝነት ይመሩታል።
በሌላኛው የ6ኛ ሳምንት የሊጉ መርሃ ግብር አስቶንቪላ ከፉልሃም ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ ይጫወታሉ።