ቀጥታ፡

የመስቀል ደመራ በዓል ልዩና አስደናቂ ሥርዓቶችን የተላበሰ ድንቅ ኃይማኖታዊ እሴት ነው -  ዓለም አቀፍ ጎብኚዎች

አዲስ አበባ፤ መስከረም 17/2018 (ኢዜአ)፡-የመስቀል ደመራ በዓል ልዩና አስደናቂ ሥርዓቶችን የተላበሰ ድንቅ የኢትዮጵያውያን ኃይማኖታዊ እሴት መሆኑን በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ በተከበረው የመስቀል ደመራ በዓል የታደሙ ዓለም አቀፍ ጎብኚዎች ገለጹ።

የመስቀል ደመራ በዓልን የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት የሳይንስና የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) አዘርባጃን ባኩ ከተማ ባካሄደው ስምንተኛ ጉባኤው ላይ የማይዳሰስ የዓለም ቅርስ አድርጎ መመዝገቡ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ኦሮቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን የአደባባይ ክብረ በዓላት ከሆኑት አንዱ የመስቀል ደመራ በዓል በአዲስ አበባና በመላው ኢትዮጵያ በድምቀት ተከብሯል።

በመስቀል አደባባይ በተከበረው የመስቀል ደመራ በዓልም ብፁዓን አባቶች፣ የመንግስት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የሀገራት አምባሳደሮችና ዓለም አቀፍ ጎብኝዎች ተገኝተዋል።

በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ በተከበረው በዓል ላይ የተገኙ ዓለም አቀፍ ቱሪስቶችም የመስቀል ደመራ ቀልብን የሚስቡና መንፈስን የሚያድሱ ውብ ኃይማኖታዊ ሥርዓቶችን የያዘ በዓል መሆኑን ገልጸዋል።

አስተያየቱን ለኢዜአ የሰጠው አሜሪካዊ ጎብኚ ርናልዶ ሔድ፤ በመጀመሪያ ጉብኝቱ የተመለከተው የኢትዮጵያ የመስቀል ደመራ በዓል አስደናቂ መሆኑን ገልጿል።


 

ኢትጵያዊያን አስደናቂ ኃይማኖታዊና ባህላዊ በዓላት በተጨማሪ ዜጎች እርስ በእርሳቸው የሚደጋገፉበት የአንድነት ድባብ የተላበሰ የአመጋገብ ሥርዓት እንዳላቸው መመልከቱን ተናግሯል።

የመስቀል ደመራ በዓል ስሜትን የሚጋባ ጥልቅ መንፈሳዊ የአንድነት ድባብ የሚስተዋልበት የኢትዮጵያዊያን ውብ የህይወት ገጽታ መሆኑን ገልጾ፤ በህይወት አንዴ በሚገኘው በዓል ላይ መገኘቱ ልዩ ደስታ እንደፈጠረለት ተናግሯል።

ሌላኛው አሜሪካዊ ጎብኚ ሚካኤል ኢፒስተን፤ የመስቀል ደመራ ደማቅ ኃይማኖታዊ ሥርዓት ማራኪ ድባብ የፈጠረ የአደባባይ በዓል መሆኑን ገልጿል።


 

በመስቀል ደመራ ኃይማኖታዊ በዓል የሚንጸባረቀው አንድነትም ኢትዮጵያውያን የባህል ሃብታም መሆናቸውን የሚያሳይና ከመንፈስ የሚጋባ ሥርዓት መሆኑን ተናግሯል።

ዓለም አቀፍ ጎብኝዎችም የሰው ልጅ መገኛ ምድር የሆነችውን ኢትዮጵያን በመጎብኘት ብዙ መልካም ነገሮችን መጋራት እንደሚችሉ አንስቷል።

እንግሊዛዊ ጎብኚ ዴቪድ ፊሊፕስ፤ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራትን ጨምሮ ከአስር ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ጉብኝት ማድረጉን አስታውሷል።


 

ኢትዮጵያም የባህል፣ የታሪክና ብዝኅነት ሃብታም መሆኗ ለቱሪዝም መዳረሻነት ጎልታ እንድትታይ ማድረጉን ገልጿል።

በኢትዮጵያ ጉብኝቱም በርካታ ጓደኞችን ማፍራቱን የገለጸው ዴቪድ ፊሊፕስ፤ የህዝቦቿ ውብ ባህሎችና ደማቅ ሥርዓቶችም ለጎብኝዎች ቀልብን የሚስቡ መሆናቸውን ተናግሯል።

ሊባኖሳዊ ጋቢ አቦንሳምራ፤ በመስቀል ደመራ በዓል ስሜቱ የሚጋባና ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው ድንቅ ኃይማኖታዊ የአደባባይ ሥርዓት መመልከቱን ገልጿል።


 

ኢትዮጵያውያን በድንቅ መንፈሳዊና ባህላዊ እሴት አሸብርቀው የሚያከብሩት የመስቀል በዓልም ከመንፈስ የሚጋባ ድንቅ ኃይማኖታዊ ቅርስ መሆኑን ተናግሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም