መስቀሉ ለዓለም ብርሃን እንዳበራ ሁሉ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ ትልቅ ብርሃን ይዞ መጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
መስቀሉ ለዓለም ብርሃን እንዳበራ ሁሉ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ ትልቅ ብርሃን ይዞ መጥቷል
አዲስ አበባ፤ መስከረም 17/2018 (ኢዜአ)፡-መስቀሉ ለዓለም ብርሃን እንዳበራ ሁሉ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ ትልቅ ብርሃን ይዞ መጥቷል ሲሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን የሃይማኖት መምህራን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን በአደባባይ የሚከበረው የመስቀል ደመራ በዓል ትናንት በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ በደማቅ ሥነ-ሥርዓት ተከብሯል።
በበዓሉ ላይ የተገኙ የሃይማኖት መምህራን ለኢዜአ እንደገለጹት፤ እንደ መስቀል ደመራው ሁሉ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ ትልቅ ብርሃን ይዞ መጥቷል።
ለረጅም ጊዜ በተለያዩ ምክንያቶች ስሟ ደብዝዞ የቆየው ኢትዮጵያ በልጆቿ የተባበረ ክንድ ታላቁ ህዳሴ ግድብን እውን በማድረግ ወደ ብርሃን እየወጣች ነው ብለዋል።
በበዓሉ የታደሙት መምህር ሽመልስ ወንድአፍራሽ እንዳሉት፤ የጌታ መስቀል ተረስቶ እና ተደብቆ እንዳልቀረ ሁሉ ኢትዮጵያም በልጆቿ ትብብር እያንሰራራች ትገኛለች ብለዋል።
መስቀሉ ለዓለም ብርሃን እንዳበራ ሁሉ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ ትልቅ ብርሃን ይዞ መጥቷል ብለዋል።
ታላቁ ህዳሴ ግድብ የመቻላችን፣ የመነሳታችን እና ዝቅ ብለን እንዳልቀረን ያስመሰከርንበትና አንድነታችንን ዳግም ያረጋገጥንበት ነው ብለዋል።
ታላቁ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያን ትንሳኤ ያረጋገጠ የመልማትና ከድህነት የመውጫ ጅማሮ መሆኑን ጠቁመዋል።
በመንበረ ጠቅላይ ፓትርያርክ ቤተክህነት የትምህርትና ማሰልጠኛ ምክትል መምሪያ ሃላፊ መልዓከ ምህረት በቃሉ ወርቅነህ በበኩላቸው፤ ለረጅም ዓመታት ኢትዮጵያውያን በቁጭት ስንመለከተው የነበረውን ግድብ በህብረት አሳክተነዋል ብለዋል።
በቀጣይ በሌሎች ስራዎች በመሳተፍ በተለይ ወጣቱ ትውልድ ለአገሩ እድገት የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ ብርሃን፣ ምልክትና የአገሪቷ መነሳት ማሳያ ነው ብለዋል።