የመስቀል ደመራ የኢትዮጵያውያን አንድነት ደምቆ የሚታይበት ልዩ በዓል ነው-የተለያዩ አገራት ዜጎች - ኢዜአ አማርኛ
የመስቀል ደመራ የኢትዮጵያውያን አንድነት ደምቆ የሚታይበት ልዩ በዓል ነው-የተለያዩ አገራት ዜጎች
አዲስ አበባ፤ መስከረም 17/2018 (ኢዜአ)፡-የመስቀል ደመራ የኢትዮጵያውያን አንድነት ደምቆ የሚታይበት ልዩ የአደባባይ በዓል መሆኑን የተለያዩ አገራት ዜጎች ገለጹ።
በኢትዮጵያ እየታየ ያለውን ፈጣን የመሰረተ ልማት ዕድገትም አድንቀዋል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን በአደባባይ የሚከበረው የመስቀል ደመራ በዓል ትናንት በአዲስ አበባ በመስቀል አደባባይ በደማቅ ሥነ-ሥርዓት ተከብሯል።
የመስቀል ደመራ በዓል በዓለም የትምህርት የሳይንስና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ) መመዝገቡን ተከትሎ ከኢትዮጵያውያን አልፎ የዓለም የማይዳሰስ ቅርስ ሆኗል።
ይህንን ተከትሎ በየዓመቱ የተለያዩ አገራት ቱሪስቶች የደመራና የመስቀል በዓላትን ለመታደም ወደ ኢትዮጵያ ይመጣሉ።
የዘንድሮው የደመራ በዓልን ለመታደም መስቀል አደባባይ ከተገኙት የውጭ አገራት ዜጎች መካከል ኬንያዊው ዊክሊቭ ኦሎ፣ስፔናዊቷ ቪኪ አንቶኒዮ እንዲሁም አርሜኒያዊው ሳርጊስ ሀሩዩኒያ ይገኙበታል።
እነርሱ እንደሚሉት የኢትዮጵያውያን የመስቀል ደመራ አከባበር ከሌሎች አገራት የተለየና የደመቀ ነው።
ኬንያዊው ዊክሊቭ ኦሎ የደመራ በዓል ላይ በርካታ የእምነቱ ተከታዮችን በአንድነት ማየት የተለየ እንደሚያደርገው ገልጾ፤ በሌሎች አገራት እንዲህ አይነት ብዛት ያለው ህዝብ አንድ ላይ ተሰባስቦ ማክበሩ የተለመደ አለመሆኑን ተናግረዋል።
የህዝቡን የአንድነት መንፈስ አድንቀው በአገራቸውም ህዝቡ በአንድነት መንፈስ ተሰባስቦ በዓል የሚያከብርበት ሁኔታ እንዲኖር ተመኝተዋል።
ስፔናዊቷ ቪኪ አንቶኒዮ እንዲሁም አርሜኒያዊው ሳርጊስ ሀሩዩኒያ የኢትዮጵያ ባህል የሚናፈቅና ልዩ ስሜት የሚሰጥ ነው ብለዋል።
የተለያዩ አገራትን የማየት አጋጣሚ እንደነበራቸውና የኢትዮጵያ የአደባባይ በዓል አከባበር ግን ከሁሉም እንደተለየባቸው የሚናገሩት ደግሞ ጀርመናዊው ኡሊ ባጅ እንዲሁም እንግሊዛዊው ዊሊያም ስሚዝ ናቸው።
ኢትዮጵያ እያስመዘገበች ያለውን ፈጣን የመሰረተ ልማት ዕድገት ያደነቁት አስተያየት ሰጪዎቹ ቱሪስቶች ባላቸው ጊዜ ኢትዮጵያን እንዲጎበኙ ጠይቀዋል።
የመስቀል ደመራ በዓል በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በድምቀት የተከበረ ሲሆን ዛሬም የመስቀል በዓል በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ እየተከበረ ይገኛል።