80ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ እና የኢትዮጵያ ተሳትፎ - ኢዜአ አማርኛ
80ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ እና የኢትዮጵያ ተሳትፎ

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ግዙፉና ጉምቱው የዓለም የብዝሃወገን ዲፕሎማሲ መድረክ ነው።
80ኛው የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ከጳጉሜን 4 ቀን 2017 ዓ.ም አንስቶ “ደህናነት በአብሮነት፤ 80 ዓመታት እና ከዚያ በላይ ለሰላም፣ ለልማት እና ለሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ” በሚል መሪ ሀሳብ እየተካሄደ ይገኛል።
የጠቅላላ ጉባኤው አካል የሆነ ከፍተኛ የምክክር እና ክርክር መድረክ ከመስከረም 13 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ እየተደረገ ነው።
ከሰላም እስከ አየር ንብረት ለውጥ፣ ከዘላቂ ልማት እስከ ዲጂታል አካታችነት፣ ከሰብዓዊነት እስከ የዓለም የኢኮኖሚ አወቃቀር፣ በዓለም መድረክ ፍትሐዊ ውክልናን ከማግኘት እስከ ዓለም በቀጣይ ምን ትሆን? ድረስ በርካታ ጉዳዮች ተነስተው ውይይቶችና ክርክሮች በማድረግ ለወደፊቱ ይበጃሉ የተባሉ ሀሳቦች በመነሳት ላይ ይገኛሉ።
በጉባኤው ይፋዊ መክፈቻ ላይ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ባደረጉት ንግግር ዓለም በተለያዩ ሰላምና ፀጥታ ጉዳዮች፣ ድህነት፣ ረሃብ፣ ጦርነት፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣የኢኮኖሚ ቀውስ እየተፈተነች ባለበት ወቅት የሚከበረው የተመድ 80ኛ ዓመት አባል ሀገራት ከመቼውም ጊዜ በላይ አብሮነታቸውን በማጠናከር የተሻለች ዓለም ለመፍጠር በጋራ መሥራት እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
የተመድ ሥርዓትንና መዋቅር 21ኛው ክፍለ ዘመን በሚመጥን ልክ መለወጥ እንደሚገባ አመልክተዋል።
ዋና ፀሐፊው ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ምርጫውን ሰላም፣ ፍትህ ዘላቂ ልማት እና ሰብአዊ ክብር ሊያደርግ እንደሚገባና ለተግባራዊነቱም ቁርጠኝነት እንዲያሳይ ጥሪ አቅርበዋል።
በፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ የተመራ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በጠቅላላ ጉባዔው ላይ ተሳትፎ እያደረገ ነው።
ልዑካን ቡድኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሃደራ አበራን ጨምሮ ከፍተኛ ባለስልጣናትን አካቷል።
ኢትዮጵያ በጉባዔው ላይ የራሷን ብሔራዊ ጥቅሞች እና የአፍሪካን ጥቅሞች በሚያስጠብቁ ጉዳዮች ላይ ንቁና ጠንካራ ተሳትፎ እንደምታደርግ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ገልጸዋል።
ከዋናው ጉባዔ ተሳትፎ በተጨማሪ በርካታ የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን የጎንዮሽ የውይይት መድረኮች ላይም ኢትዮጵያ የራሷን ብሄራዊ ጥቅሞች ቅድሚያ እየሰጠች እንደምትሳተፍም አመልክዋል።
ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ከጉባኤው ጎን ለጎን ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ጋር ተወያይተዋል።
ዋና ፀሐፊው ኢትዮጵያ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አጠናቃ በመመረቋ ፣ የአየር ንብረት ጉባዔ እና ሌሎች ፕሮጀክቶችን በማስተናገድ ላስመዘገበችው ስኬት እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።
ሁለቱ ወገኖች በቀጣናው እና በሌሎች ጉዳዮች ላይም ተወያይተዋል።
በተጨማሪም ፕሬዝዳንቱ ከተመድ ጠቅላላ ጉባዔ ፕሬዝዳንት አናሌና ባርቦክ ጋር ተወያይተዋል።
ሁለቱ መሪዎች በወቅታዊ ዓለም አቀፍ ተግዳሮቶች እና በባለብዙ ወገን ግንኙነት ላይ እያሳደረ ስለሚገኘው ተጽዕኖ ሀሳቦችን ተለዋውጠዋል።
ፕሬዝዳንት ታዬ የባለብዙ ወገን ግንኙነት እና የጋራ ደኀንነት መርሆዎችን ለማስጠበቅ የጋራ ጥረቶችን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።
በቅርቡ የተመረቀው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት የተመድ ዘላቂ ልማት ግቦችን ከማሳካት ረገድ በተለይም ግብ ሰባትን ለማሳካት ግድቡ ንጹሃ የኃይል አቅርቦት ከማሳደግ አኳያ ያለውን ፋይዳ ገልጸዋል።
ፕሬዝዳንት አናሌና ባርቦክ በበኩላቸው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቻርተር መርሆዎችን ማክበር እና መጠበቅ ለዓለም ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።
ሁለቱ ወገኖች በኢትዮጵያ ልማት፣ ቀጣናዊ ሰላም እና ደኀንነትን ጨምሮ በተለያዩ ቀጣናዊ የትኩረት መስኮች ላይም መክረዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሃደራ አበራ ከጉባኤው ጎን ለጎን ከተለያዩ ሀገራት እና ተቋማት ጋር የሁለትዮሽ ውይይቶችን እያደረጉ ይገኛል።
አምባሳደር ሃደራ ከደቡብ ሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መንደይ ሲማያ ኩምባ የኢትዮጵያ እና ሱዳን የሁለትዮሽ ኢኮኖሚያዊ ግፍንኙነት ማጠናከር እንዲሁም በቀጣናዊ እና በባለብዙ ወገን የትብብር መድረኮች የተባበረ አቋም እንዲኖራቸው ማድረግ በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ መክረዋል።
ከሞዛምቢክ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማሪያ ማኑኤላ ዶስ ሳንቶስ ሉቃስ ጋርም ተወያይተዋል።
ሽብርተኝነትን መከላለከል፣ አቪዬሽን እና ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
አምባሳደሩ ከአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ከፍተኛ ባለሥልጣን አምባሳደር ጆናታን ፕራት ጋር በሀገራቱ የጋራ ፍላጎቶች ላይ ተወያይተዋል።
ሁለቱ ወገኖች በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን የንግድ ግንኙነት ማሻሻል የሚያስችሉ ሥራዎችን ለማከናወን ተስማምተዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው ከአውሮፓ ከአውሮፓ ሕብረት የውስጥ ጉዳይ እና የፍልሰት ኮሚሽነር ማግነስ ብሩነር ጋርም የተወያዩ ሲሆን ሁለቱ ወገኖች ዓለም አቀፍ ፈተና በሆኑ ከፍልሰት ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ ለመስራት ቁርጠኝነታቸውን ገልጸዋል።
አምባሳደሩ ከተባበሩት አረብ ኢምሬቶች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሼክ ሻክቦት ቢን ናህያን አል ናህያን ጋር የሁለትዮሽ ግንኙነቱ የበለጠ በሚያጠናክሩ ዕድሎች እንዲሁም በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን የንግድ እና ኢንቨስትመንት ትብብር የበለጠ ማሳደግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል።
አምባሳደር ሃደራ አበራ ከኩባ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ብሩኖ ሮድሪጌዝ ፓሪላ ጋር በሁለትዮሽ ትብብር ዙሪያ መክረዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው ከአዘርባጃን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጄሁን ቤራሞቭ ጋር ባደረጉት የሁለትዮሽ ውይይት ኢትዮጵያና አዘርባጃን ጠንካራ ግንኙነት ያላቸው አገራት መሆናቸውን በመጥቀስ ሁለቱ አገራት በተለይ በኢኮኖሚ ዘርፎች ይበልጥ ተቀናጅተው ሊንቀሳቀሱ እንደሚገባ ገልፀዋል።
ሁለቱ ወገኖች በውይይታቸው ሀገራቱ በንግድ፣ በኢንቬስትመንት፣ በቱሪዝም በግብርናና በትምህርት ዘርፎች እንዲሁም በባለብዙ ወገን መድረክ ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር በጋራ ለመሥራት ተስማምተዋል።
ኢትዮጵያ ከጠቅላላ ጉባኤው ጎን ለጎን ባሉ የጎንዮሽ ውይይቶች ላይ እየሳተፈች ይገኛል።
ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ በተሳተፉበት መድረክ ኢትዮጵያ የአፍሪካን የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነት ማስፋት አላማ ያደረገው “Mission 300” ኢኒሼቲቭ ተቀላቅላለች።
በዓለም ባንክ እና በአፍሪካ ልማት ባንክ የሚመራው ኢኒሼቲቭ እ.አ.አ በ2030 በአፍሪካ የሚገኙ 300 ሚሊዮን ዜጎችን በኤሌክትሪክ ኃይል የማስተሳሰር ውጥን ያለው ነው።
ፕሮጀክቱ የአፍሪካ መንግስታት፣ የግሉ ዘርፍ እና የልማት አጋሮችን ያሳተፈ ሲሆን በአፍሪካ አስተማማኝነቱ የተረጋገጠ፣ አካታች እና ተመጣጣኝ የኢነርጂ አቅርቦትን ተደራሽ በማድረግ የኢኮኖሚ እድገት እና ቀጣናዊ ትስስርን የማጠናከር አላማንም አንግቧል።
ኢኒሼቲቩ ኢትዮጵያ በታዳሽ ኃይል ያላትን እምቅ አቅም ለመጠቀም እና ቀጣናዊ የኃይል ትስስሯን ለማሳደግ ወሳኝ ሚና እንዳለው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ የንጹህ ኢነርጂ ሽግግር ውስጥ ያላትን የመሪነት ሚና እንደሚያሳድግና አፍሪካ ከኢነርጂ ድህነት የማላቀቅ እና ዘላቂ ልማትን የማረጋገጥ ትልም ለማሳካት እንደሚያግዝም ገልጿል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሃደራ አበራ በአፍሪካ በሽታ መከላከል እና መቆጣጠር ማዕከል (ሲዲሲ አፍሪካ) ኮሚቴ አባል የመሪዎች ስብሰባ ላይ ተሳትፈዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው በስብሰባው ላይ ኢትዮጵያ የጤናን ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ የሀገር ውስጥ የሀብት ማሰባሰብ እና ፈጠራ የተሞላበት የፋይናንስ ግኝት እንደምትከተል አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በጠቅላላ ጉባኤው ብሔራዊ ጥቅሞች እና የአፍሪካን ጥቅሞች በሚያስጠብቁ ጉዳዮች ላይ ንቁና ጠንካራ ተሳትፎ ማድረጓን እንደምትቀጥል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው ገልጸዋል።
በጉባኤው ላይ የኢትዮጵያን ልዑክ የመሩት ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ የጉባኤው አካል በሆነው ከፍተኛ የምክክር እና ክርክር መድረክ ላይ ንግግር አድርገዋል።
ፕሬዝዳንቱ በንግግራቸው በመልክዓ ምድራዊ ሁኔታዎች ምክንያት የትኛውም ሀገር የእድገት፣ የፋይናንስ እና የቴክኖሎጂ ዕድሎች ዝግ መሆን የለበትም ሲሉ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ከሌሎች ሀገራት ጋር በመሆን በቀይ ባሕር እና በሕንድ ውቅያኖስ አካባቢ የሚገኙ ሁሉም ሀገሮች እኩል ልማት እና ደኀንነትን ማረጋገጥ ወደሚያስችል ሁለንተናዊ አሠራር እንዲዘረጋ ትሠራለች ብለዋል።
ኢትዮጵያ ይህንን ሕጋዊ ፖሊሲዋን ለማሳካትም የዲፕሎማሲያዊ እና ሰላማዊ አማራጮችን እንደምትከተል አረጋግጠዋል።
በሌላ በኩል ፕሬዝዳንቱ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤትን ለማሻሻል አስቸኳይ እርምጃ እንዲወሰድ ጠይቀዋል።
በማሻሻያውም ለአፍሪካ ውክልና በምክር ቤቱ በሁለቱም በኩል ቅድሚያ እንዲሰጥ ጥሪ አቅርበው፤ ለአፍሪካ የረጅም ጊዜ የፍትሕ መሻት ጥያቄ አቋራጭ ወይም ግማሽ መፍትሔ እንደሌለ አስገንዝበዋል።
ከታላቁ ኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘም፤ የናይል ወንዝ የትብብር ማዕቀፍ በፈረንጆቹ ጥቅምት 2024 ወደ ተግባር መግባቱን እና የናይል ወንዝ ተፋሰስ ኮሚሽን ወደ መቋቋም ደረጃ መቃረቡን አስረድተዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ተጠናቅቆ መመረቁ፤ በኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽ ላልሆኑ ኢትዮጵያውያን ንጹህ የኃይል ምንጭ እንዲያገኙ የሚያደርግ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ግድቡ በከባድ የውኃ እጥረት ውስጥ ለሚኖሩ ወገኖቻችን ንጹህ ውኃ ለማቅረብ፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እና አጠቃላይ ልማትን እውን ለማድረግ አቅማችንን ያሳድጋል ብለዋል ፕሬዚዳንቱ።
ግድቡ ለሰፋፊ ክልላዊ ትስስር ተስፋን የሚፈጥር መሆኑንም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ እ.አ.አ 1945 የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሲመሰረት መስራች አባል ከነበሩት ሀገራት መካከል አንዷ ናት።
ይህም ኢትዮጵያ የባለብዝሃ ወገን እና ዓለም አቀፍ ትብብር ያላትን የማይናወጥ አቋም እና የጸና ቁርጠኝነት በግልጽ የሚያሳይ ነው።
ኢትዮጵያ በዘንድሮው ጉባኤ ሰላም፣ ደህንነት፣ ዘላቂ ልማት እና የአየር ንብረት ለውጥን ጨምሮ በዓለም አንገብጋቢ ጉዳዮች ላይ ያራሷ እና የአፍሪካን ድምጽ በማሰማት የነቃ ተሳትፎ እያደረገች ትገኛለች።
80ኛው የተመድ ጠቅላላ ጉባዔ መስከረም 19 ቀን 2018 ዓ.ም ይጠናቀቃል።