ቀጥታ፡

በታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ያሳየነውን ህብረት በሌሎች ሀገራዊ ፕሮጀክቶችም ልንደግመው ይገባል

አዲስ አበባ፤ መስከረም 17/2018 (ኢዜአ)፡-በታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ያሳየነውን ህብረት የኢትዮጵያን ከፍታና ማንሰራራት በሚያረጋግጡ ሌሎች ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ላይም ልንደግመው ይገባል ሲሉ በመስቀል ደመራ የተገኙ የበዓሉ ታዳሚዎች ገለጹ።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን በአደባባይ የሚከበረው የመስቀል ደመራ በዓል ትናንት በአዲስ አበባ በመስቀል አደባባይ በደማቅ ሥነ-ሥርዓት ተከብሯል።

በክብረ በዓሉ ላይ የተገኙ የበዓሉ ታዳሚዎች ለኢዜአ እንደገለጹት እንደ መስቀል ደመራው ኢትዮጵያውን ተደምረን የኢትዮጵያን ከፍታ የሚያረጋግጡ የልማት ስራዎች ላይ በጋራ ልንሳተፍ ይገባል። 

የበዓሉ ታዳሚ ወጣት ፋንታሁን ወርቄ እንዳለው ያሉንን የተፈጥሮ ጸጋዎች በመጠቀም አገራችንን ወደ ብልጽግና ለማሸጋገር በጋራ መስራት አለብን።


 

የዘንድሮው የደመራ በዓል ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ባስመረቅንበት ማግስት መከበሩ ልዩ እንደሚያደርገው ገልጾ፤የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የበኩሉን እንደሚወጣ ተናግሯል።

በአገር አቀፍ ደረጃ የተያዙ የግዙፍ ፕሮጀክቶች ግንባታ እንዲሳካ የበኩሌን እወጣለሁ ያሉት ደግሞ የበዓሉ ተሳታፊ ወይዘሮ ሶስና ካሳሁን ናቸው።


 

አገራችንን ወደ ቀጣይ ምዕራፍ ለማሸጋገር፣ በጋራ ለማሳደግ እና ለሁሉም የተመቸች አገር ለመፍጠር የምንሰስተው ነገር ሊኖር አይገባም ብለዋል።

ዲያቆን እሱባለው ኩምሳ በበኩሉ በአገር አቀፍ ደረጃ የተጀመሩ ግዙፍ የልማት ሥራዎች እንዲሳለጡ ርብርባችንን ማጠናከር አለብን ብሏል።


 

ሁላችንም በህብር ተደምረንና በአንድነት ቆመን የአገራችንን ልማት ለማረጋገጥ በጋራ መስራት አለብን ሲል ተናግሯል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም