ቀጥታ፡

ሕዳሴ ግድብ አፍሪካን የሚቀይር ፕሮጀክት ነው -አሜሪካዊቷ ጋዜጠኛ አን ጋሪሰን

አዲስ አበባ፤ መስከረም 17/2018 (ኢዜአ)፦ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አፍሪካን የሚቀይር እና ቀጣናዊ ትስስርን የበለጠ የሚያጠናክር ፕሮጀክት መሆኑን አሜሪካዊቷ ጋዜጠኛ እና ፀሐፊ አን ጋሪሰን ገለጸች።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ጳጉሜን 4 ቀን 2017 ዓ.ም በይፋ መመረቃቸው ይታወቃል።

ሕዳሴ ግድብ ከኢትዮጵያ ባለፈ ለአፍሪካ እድገት እና ልማት መስፈንጠሪያ የሚሆን ትልቅ አቅም የያዘ ነው።

አሜሪካዊቷ ጋዜጠኛ እና ፀሐፊ አን ጋሪሰን ከኢዜአ ጋር ባደረገችው ቆይታ ሕዳሴ ግድብ በመመረቁ እጅጉን መደሰቷን ገልጻለች።

ኢትዮጵያውያን ለፈተናዎች እና ለችግሮች ሳይበገሩ በራሳቸው ፋይናንስ እና ጉልበት ሕዳሴ ግድብን መገንባታቸው ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑንም ተናግራለች።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዓለማችን ላይ ዜጎች የውጭ እርዳታን ሳይጠብቁ በራሳቸው ጥሪት ከገነቧቸው ግዙፍ ፕሮጀክቶች አንዱ ሆኖ የሚጠቀስ መሆኑንም ገልጻለች።

ግድቡ የኢትዮጵያውያን የኑሮ ሁኔታ በመቀየር፣ የኢንዱስትሪ ዘርፍን በማሳደግ እና የኢኮኖሚ እድገትን በማሳለጥ ረገድ ያለው ሚና ወሳኝ መሆኑን ነው የጠቀሰችው።

ሕዳሴ አፍሪካ ያለባትን የኢነርጂን እጥረት በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚቀይር የገለጸችው ጋዜጠኛዋ ይህም ለኢኮኖሚ እድገት እና ቀጣናዊ ትስስር እንዲሳለጥ ያደርጋል ብላለች።

የአፍሪካ ሀገራት ወደ ውጭ የሚልኩትን ጥሬ እቃ በአነስተኛ ዋጋ በመሸጥ ያንኑ ግብአት እሴት ተጭምሮ መልሰው በከፍተኛ ዋጋ የሚገዙበትን የኢኮኖሚ ወጥመድ ለማስቀረት የኤሌክትሪክ ኃይል ወሳኝ ሚና እንዳለው ገልጻ፤ ሕዳሴ ግድብ ከዚህ አንጻር ጉልህ አበርክቶ ይኖረዋል ነው ያለችው።

ሕዳሴ ግድብ የአፍሪካ ሀገራት ወደ ታዳሽ የኃይል ምንጭ ለሚያደርጉት ሽግግር በምሳሌነት የሚጠቀስ ፕሮጀክት መሆኑንም ገልጻለች።

ግድቡ የታዳሽ ኃይል ምንጭ መሆኑ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ልማት እና እድገት ቁልፍ ሚና እንዳለው ተናግራለች።

ኢትዮጵያ በውሃ ሀብቷ ተጠቅማ የመልማት መብት አላት ያለችው ጋዜጠኛ አን በናይል ዋንዝ አብዛኛው ድርሻ ያላት ሀገር በሀብቷ የመጠቀሟ ጉዳይ ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም ብላለች።

የቀጣናው እና የአፍሪካ ሀገራት ውሃን ጨምሮ ሌሎች ሀብቶቻቸውን በትብብር መንፈስ በመጠቀም የጋራ ልማት እና እድገታቸውን እንዲያረጋግጡም አመላክታለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም