የቅመማቅመም ጥራትን ለማስጠበቅ እየተሠራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የቅመማቅመም ጥራትን ለማስጠበቅ እየተሠራ ነው
አዲስ አበባ፤ መስከረም 17/2018(ኢዜአ)፡- የቅመማቅመም ጥራትን ለማስጠበቅ ከዘር ዝግጅት እስከ ኤክስፖርት ድረስ ባለው ዕሴት ሰንሰለት በርካታ ተግባራት በጋራ እየተከናወኑ መሆኑ የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለስልጣን ገለጸ።
የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር እና የልማት ዘርፍ ኃላፊ ታጋይ ኑሩ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የቅመማቅመም የ10 ዓመት ስትራቴጂ ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ ተገብቷል።
በዚህ መሠረትም የቅመማቅመም ኤክስቴንሽን አሠራርን ለማሻሻል እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰው፣ ለ19 የቅመማቅመም ዓይነቶች የፓኬጅ ማሻሻያ መደረጉን አንስተዋል።
በፓኬጁ መሰረት ቅመማቅመም አብቃይ ለሆኑ የክልልና የዞን ከፍተኛ ባለሙያዎች ስልጠና መሰጠቱን ገልጸዋል።
የጥራትና ግብይቱን ሥራ ለማቀላጠፍና ቁጥጥር ውስጥ በማስገባት መምራት የሚያስችል የቅመማቅመም የጥራትና ግብይት መመሪያ ጸድቆ ወደ ሥራ መግባቱን አስረድተዋል።
ይህን መመሪያም ወደ አዋጅ ከፍ ለማድረግ ረቂቁ አልቆ ወደ ግብርና ሚኒስቴር መላኩን ነው የገለጹት።
በ10 ዓመት ስትራቴጂው መሠረት፤ ዘርፉን በሚፈለገው ልክ ለማሳደግ ከዘር ጀምሮ በቅንጅት መሥራት የሚያስችል ዐቅም ይገነባል ብለዋል።
በዘርፉ ዘር አባዦች የሌሉ በመሆኑ በዚህ ዘርፍ ከክልሎችና ከግብርና ምርምር ጋር በመተባበር በቀጣይ እንደሚሠራም አመላክተዋል።
የዕሴት ሰንሰለቱን የማሳጠርና ምርት በጥራት ተመርቶ ወደ ማዕከላዊ ገበያ እንዲደርስ ይሠራል ብለዋል።
በምርት አሰባሰብ፣ አዘገጃጀትና ማቀነባበርያ ላይ የሚታዩ ተግዳሮቶች እንዲወገዱና ዘመናዊ የድኅረ ምርት ማዘጋጃና ማቀነባበሪያ ዘዴዎችን በስፋት እንዲጠቀሙ ይሠራል ነው ያሉት።
ቅንጅታዊ አሠራርን በማጠናከር፣ ምርምርን በማሳደግ፣ የሀብት ዐቅምን በማሰባሰብ፣ የግንዛቤ ችግርን በመቅረፍና የአቅርቦት መጠኑን ከጥራት ጋር በማሻሻል በሚፈለገው ልክ ኤክስፖርት በማድረግ ሀገርን መጥቀም እንደሚቻል አስረድተዋል።