ቀጥታ፡

የመስቀል ደመራ በዓልን ስናከብር ለሀገር ሰላም እና ዕድገት ተሳትፏችንን ለማጠናከር በመነሳሳት ሊሆን ይገባል- የሃይማኖት አባቶች

ጂንካ/አርባምንጭ / ዲላ/ ወላይታ ሶዶ/(ኢዜአ)፡- በዓለም ቅርስነት የተመዘገበው  የመስቀል ደመራ በዓልን ስናከብር ለሀገር ሰላም እና ዕድገት ተሳትፏችንን ለማጠናከር በመነሳሳት ሊሆን ይገባል ሲሉ የሃይማኖቱ አባቶች  ገለጹ። 

የመስቀል ደመራ በዓል በጂንካ፣ አርባምንጭ፣ ዲላና ወላይታ ሶዶ ከተሞች በድምቀት ተከብሯል። 

በጂንካው በዓል ላይ የደቡብ ኦሞ እና የአሪ ዞን ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅድስት ስላሴ ካቴዴራል ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት  አቡነ ፊልጶስ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ከመስቀሉ ሰላምን፣ ፍቅርን፣መተሳሰብን እንማራለን ብለዋል።

በመስቀሉ ያገኘነውን ሰላምና ፍቅር በተግባር ማሳየት ይኖርብናል ሲሉ ገልጸዋል።


 

የአሪ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብረሃም አታ በበኩላቸው፣ እርስ በርስም በመያያዝ በአካባቢያችን እየተከናወኑ ያሉ ትልልቅ የልማት ስራዎችን በማጠናከር ለሀገራዊ ማንሰራራት የሚጠበቅብንን መወጣት ይገባናል ሲሉ ተናግረዋል።

የጂንካ ከተማ ከንቲባ አቶ ሲሳይ ጋልሺ፥ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በአርባ ምንጭ በተከበረው በዓል ላይ የጋሞ እና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ስኖዶስ አባል አቡነ ኤሊያስ እንደገለጹት፤  ምእመናን ፈጣሪ ለሰው ልጆች ዋጋ የከፈለበትን መስቀል እያሰቡ ለሀገር ሰላምና ልማት አርአያ ሊሆኑ ይገባል። 


 

በተለይ በየጊዜው እየተሰጠ ያለውን ቅዱስ ቃል መሠረት በማድረግ ያላቸውን ፍቅር፣ አንድነትና አብሮነት በማጽናት በሀገር ልማትና ሰላም ስራዎች ላይ  ተሳትፏችንን ማጠናከር አለብን ብለዋል።

የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ደምስ አድማሱ (ዶ/ር) በበኩላቸው የብርሃነ መስቀል በዓሉ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ባጠናቀቅን ማግስት በመሆኑ ልዩ ስሜት የሚፈጥር ነው ብለዋል።

የአርባምንጭ ከተማ ከንቲባ መስፍን መንዛ (ዶ/ር)፤  መስቀል በዓል በአዲስ ዓመት ማግስት የሚከበር በዓል እንደመሆኑ በአዲስ መንፈስ በተሠማራንበት መስክ ለውጤት ልንተጋ ይገባል ብለዋል።


 

በዲላው በዓል ላይ የጌዴኦ፣ ኮሬና ቡርጂ ሃገረ ስብከት ጳጳስ አቡነ ገሪማ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የመስቀል ደመራ እውነተኛው የክርስቶስ ደም የፈሰሰበበት መስቀል ደብዛው ከጠፋበት በፅኑ ፍለጋና ጥረት የተገኘበት ማብሰሪያ መሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም ከደመራው ጥምረትን ከመስቀሉ ፍቅርን በመማር አንድነታችንን ለላቀ ልማትና እድገት ልንጠቀመው ይገባል ብለዋል።

''የመስቀል ደመራ በዓል ከሃይማኖታዊ ይዘቱ በተጨማሪ የማህበራዊ አንድነታችን ምልክት ነው'' ያሉት ደግሞ የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዝናቡ ወልዴ ( ዶ/ር ) ናቸው።

የመስቀሉን እውነተኛ ሃሳብ በመረዳትና በተግባር በመኖር ለፍቅርና ለሰላም መጽናት የሚጠበቅብንን ልንወጣ ይገባል ያሉት ደግሞ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክ ተዋህዶ ቤተክርስተያን የወላይታ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ  እና የቅዱስ ስኖዶሱ አባል አቡነ ይስሐቅ ናቸው።


 

መስቀል የተበተነን የሰበሰበ የፍቅር መግለጫ በመሆኑ ሁላችንም ከመስቀሉ የተማርነውን የመተሳሰብና የመደጋገፍ ኢትዮጵያዊ  ፍቅራችንን ማሳየት አለብን ብለዋል።

በበዓሉ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ሳሙኤል ተሰማ (ረዳት ፕሮፌሰር) የደመራ በዓል መሰብሰብ በጉልህ የተገለጠበት ኃይማኖታዊ በዓል ነው ብለዋል።

እንደደመራ በመደመር አሰባሳቢ ገዢ ትርክት በማስረጽ እውነተኛ የመስቀሉ ወዳጆች መሆናችንን በአንድነታችን መግለጥ እንደሚገባም አሰገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም