የመስቀል ደመራ በዓል ለሰው ልጆች ሁሉ የእርቅና ሰላም መገለጫ ተደርጎ የሚወሰድ የፍቅርና አብሮነት መገለጫ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የመስቀል ደመራ በዓል ለሰው ልጆች ሁሉ የእርቅና ሰላም መገለጫ ተደርጎ የሚወሰድ የፍቅርና አብሮነት መገለጫ ነው
አዳማ፣ ጭሮ መስከረም 16/2018 /ኢዜአ/፡-የመስቀል ደመራ በዓል ለሰው ልጆች ሁሉ የእርቅና ሰላም መገለጫ ተደርጎ የሚወሰድ የፍቅርና አብሮነት መገለጫ መሆኑን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የቅዱስ ሲኖዶስ አባልና የምስራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጎርጎሪዮስ ገለጹ።
የመስቀል ደመራ በዓል የሃይማኖት አባቶች፣ በርካታ ምእመናን፣ የውጭና የሀገር ውስጥ ቱሪስቶች በተገኙበት በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ተከብሯል።
በዓሉ በኦሮሚያ ክልል አዳማ እና ጭሮ ከተሞችም በደማቅ ስነ ስርአት ተከብሯል።
በአዳማ በተካሄደው ክብረ በዓል ላይ መልእክት ያስተላለፉት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የቅዱስ ሲኖዶስ አባልና የምስራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጎርጎሪዮስ፤ የመስቀል ደመራ በዓል ለሰው ልጆች ሁሉ የእርቅና ሰላም መገለጫ ተደርጎ የሚወሰድ የፍቅርና አብሮነት መገለጫ መሆኑን አንስተዋል።
በመሆኑም የመስቀል በዓል የተለያዩትን የሚያሰባስብ እና የተጣሉትን የሚያስታርቅ የሰላምና የእርቅ ተምሳሌት በመሆኑ በዚሁ መልኩ አስበን ማክበር አለብን ብለዋል።
የአዳማ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ንጋቱ ሞትማ፤ የመስቀል ደመራ በዓል የሰላምና የፍቅር እሴት መገለጫ በመሆኑ ትውፊቱን ጠብቆ መዝለቅ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
በተመሳሳይ በዓሉ በምዕራብ ሀረርጌ ዞን ጭሮ ከተማ በርካታ ታዳሚዎችና የእምነቱ ተከታዮች በተገኙበት ተከብሯል።
የምዕራብ ሐረርጌ ሊቀጳጳስ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ እንጦስ፤ በዚሁ ጊዜ ባደረጉት ንግግር የመስቀል ደመራ በዓል ስናከብር ፍቅርን፣ ሰብአዊነትንና አብሮነትን በማጠናከር መሆን አለበት ብለዋል።
የቤተክርስቲያን አስተምህሮና የመስቀሉ አላማ ፍቅር በመሆኑ የሃይማኖት አባቶች ምእመናቸውን በማስተማር መልካም ስራ እንዲሰሩ በማድረግ መትጋት እንዳለባቸውም አንስተዋል።