ቀጥታ፡

ኢትዮጵያና ቻይና በዲጂታል ቴክኖሎጂ ዘርፍ ትብብራቸውን የበለጠ ያጠናክራሉ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 16/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያና ቻይና በዲጂታል ቴክኖሎጂ ዘርፍ ትብብራቸውን የበለጠ እንደሚያጠናክሩ አረጋገጡ።

ሁለቱ አገሮች በዲጂታል ቴክኖሎጂ ዘርፍ በጋራ መስራት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርገዋል።

በውይይቱ ወቅት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር)፤ ኢትዮጵያ ለዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች መሆኑን አብራርተዋል።

በቅርቡ የተመረቀው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ጨምሮ ትላልቅ የልማት ፕሮጀክቶችን ውጤታማ በሆነ መንገድ እየፈጸመች መሆኑን አመልክተው፤ ለዚህ ደግሞ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ጉልህ ፋይዳ እንዳለው አንስተዋል።

የኢትዮ-ቻይና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ወደ ስትራቴጂክ አጋርነት መቀየሩን ገልጸው፤ ዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ላይም ትብብራቸውን የበለጠ ያጠናክራሉ ብለዋል።

ኢትዮጵያ የዲጂታል ቴክኖሎጂን ዋነኛ የልማት አጀንዳ በማድረግ እየሰራች መሆኑን ጠቁመው፤ የመንግስት አገልግሎትን ጨምሮ በርካታ የዲጂታል መሰረተ ልማቶች እየተገነቡ መሆኑን ተናግረዋል።

ዘርፉ የዜጎችን ኑሮ ለማቃለልና የምጣኔ ሀብት ዕድገት ለማስመዝገብ ያለውን ወሳኝ ሚና በመረዳት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ውጤትም እየተገኘ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለው የዲጂታል ቴክኖሎጂ ሥርዓት ግንባታን በፖሊሲና ስትራቴጂ ደግፋ እየተገበረች መሆኑንም ነው ያብራሩት።

ኢትዮጵያና ቻይና በዘርፉ ያላቸውን ትብብር የበለጠ እንደሚያጠናክሩ አረጋግጠዋል።

የቻይና ኢንዱስትሪ፣ ኢንፎርሜሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ሊ ሌቸንግ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ ቻይና ከአፍሪካ ጋር ያላትን ግንኙነት የበለጠ ማጠናከር ትፈልጋለች።

የኢትዮጵያና ቻይና የረጅም ጊዜ ግንኙነት ውጤታማና በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ መሆኑንም አንስተዋል።

ሁለቱ አገራት በዲጂታል ቴክኖሎጂ ላይ ያላቸውን ልምድ መቀያየራቸው ስትራቴጂክ አጋርነታቸው የበለጠ ውጤታማ እንዲሆን ያደርገዋል ብለዋል።

ቻይና በዲጂታል መሰረተ ልማት ግንባታ የካበተ ልምድ እንዳላት ገልጸው፤ ከዚህ አኳያ ለኢትዮጵያ ልምዷን ታጋራለች ብለዋል።

ዲጂታል ሥነ ምህዳርን ማሳደግ ለሁሉም ዘርፎች ዕድገት ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ በአገራዊ የልማት ዕቅዶቿ ለቴክኖሎጂ ዘርፉ የሰጠችውን ትኩረት አድንቀዋል።

ሁለቱ አገሮች በዲጂታል ቴክኖሎጂ ዘርፍ በጋራ ለመስራት ስምምነት ተፈራርመዋል።

የሁለትዮሽ ሥምምነቱ በዘርፉ የሁለቱን አገራት ዜጎች የበለጠ ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑንም ተገልጿል።

ኢትዮጵያ በዲጂታል ቴክኖሎጂ ግንባታ ከቻይና ጋር አብሮ ለመስራት  ያደረገችው የሁለትዮሽ ስምምነት የአገራቱ ወዳጅነት የበለጠ እንደሚያጠናክር ተጠቁሟል።

የመግባቢያ ሥምምነቱን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ በለጠ ሞላ (ዶ/ር) እና የቻይና ኢንዱስትሪ፣ ኢንፎርሜሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ሊ ሌቸንግ (Li lechenge) ተፈራርመዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም