ቀጥታ፡

በመላው ሀገሪቱ የተከበረው የመስቀል ደመራ በዓል በሰላምና በስኬት ተጠናቀቀ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 16 /2018(ኢዜአ):- በዛሬው ዕለት አዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ በመላው ሀገሪቱ የተከበረው የመስቀል ደመራ በዓል በሰላምና በስኬት መጠናቀቁን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከሌሎች የፀጥታና ደኅንነት ኃይሎች ጋር በመቀናጀት በመላው ሀገሪቱ በቴክኖሎጂ የታገዘ በርካታ የፖሊስ ሠራዊት በማሰማራት፤ ከህዝብ፣ ከሃይማኖት መሪዎች፣ ከበዓሉ አዘጋጅ ኮሚቴዎችና ከወጣቶች ጋር ተባብሮ በመስራቱ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች በዓሉ ያለምንም የፀጥታ ችግር በሰላም እንዲጠናቀቅ ማስቻሉን ገልጿል።


 

በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላደረገው ህዝብ፣ ለሀይማኖት መሪዎች፣ ለበዓሉ አስተባባሪ ኮሚቴዎች፣ ለወጣቶች እና በተለይ የተሰጣቸውን ግዳጅ በሚገባ ለተወጡት ለመላው የሀገራችን የፀጥታና ደኅንነት ኃይሎች ምስጋና አቅርቧል።

ህብረተሰቡ የአካባቢውን ሰላም በመጠበቅ እያሳየ ያለውን ቀና ትብብር በቀጣይ በሚከበሩት የሆራ ፊንፊኔ እና የሆረ አርሰዲ የኢሬቻ በዓላት ላይም አጠናክሮ እንዲቀጥል የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም