ቀጥታ፡

የመስቀል ደመራ በዓልን ስናከብር የመደጋገፍና የአብሮነት እሴቶቻችንን በማጠናከር መሆን አለበት

ጋምቤላ፤ መስከረም 16/2018(ኢዜአ)፡-  የመስቀል ደመራ በዓልን ስናከብር የመደጋገፍና የአብሮነት እሴቶቻችንን በሚያጠናክር መልኩ ሊሆን እንደሚገባ የጋምቤላ፣ የአሶሳ፣ የቄለም ወለጋ፣ የምዕራብ ወለጋ፣ የምስራቅ ወለጋና የሆሩ ጉዱሩ ወለጋ እና የደቡብ ሱዳን አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሩፋኤል አሳሰቡ። 

የመስቀል ደመራ በዓል ኃይማኖታዊ እሴቱን በጠበቀ መልኩ በጋምቤላ ከተማና አካባቢው በድምቀት ተከብሯል። 


 

ብፁዕ አቡነ ሩፋኤል በክብረ በዓሉ ላይ እንዳሉት፤ ምዕመኑ የአብሮነት እሴቱን በማጠናከርና የተቸገሩትን በመደገፍ በዓሉን በአንድነት ማክበር አለበት። 

የመስቀል ደመራ በዓል የፍቅር፣ የአንድነት፣ የነፃነትና የትብብር እሴት ዋነኛ ማሳያ መሆኑንም ገልጸው፤ መስቀልን የሚያውቅ ፍቅር፣ አንድነትንና ትብብርን ያጠናክራል ብለዋል።

በመሆኑም ምዕመኑ በዓሉን ሲያከብር ይህንኑ ታሳቢ ባደረገ መልኩ ሊሆን እንደሚገባ አስገንዝበዋል። 

የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አለሚቱ ኡሞድ፣ ኢትዮጵያ የሀይማኖት መቻቻልና መደጋገፍ የሚታይባት ሀገር ናት ብለዋል።


 

በየዓመቱ በታላቅ ድምቀት የሚከበረው የመስቀል ደመራ ከሀይማኖታዊ እሴቱ ባለፈ በአለም አቀፍ ደረጃ በማይዳሰስ ቅርስነት የተመዘገበና ለቱሪዝም ኢንዱስትሪው ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ የሚገኝ በዓል መሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም ይህንን እሴት በመጠበቅ ለቀጣይ ትውልድ ልናስተላልፍ ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።

በአደባባይ የሚከበሩ ሀይማኖታዊና ህዝባዊ በዓላት የሕዝቦችን አንድነትና አብሮነት በማጠናከር ረገድ ሚናቸው የላቀ መሆኑንም ገልፀዋል። 

የዘንድሮው የመስቀል ደመራ በዓል የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በኢትዮጵያውያን የጋራ ጥረት በስኬት ተጠናቆ በተመረቀበት ማግስት መከበሩ ልዩ ያደርገዋል ነው ያሉት። 

የመስቀል ደመራ በዓል ኃይማኖታዊና ባህላዊ ትውፊቱን በጠበቀ መልኩ በጋምቤላ ከተማና አካባቢው በርካታ ምዕመናንና የተለያዩ እንግዶች በተገኙበት በድመቀት ተከብሯል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም