ቀጥታ፡

መስቀል ይቅርታና እርቅን፣ እኩልነትና አንድነትን ማረጋገጥ መሆኑን በመገንዘብ ለሀገር ከፍታ በአንድነት መስራት ይገባል - ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 16/2018(ኢዜአ)፦ መስቀል ይቅርታና እርቅን፣ እኩልነትና አንድነትን፣ ፍትህና ርትዕን ማረጋገጥ መሆኑን በውል በመገንዘብ ለሀገር ከፍታ በአንድነት መስራት እንደሚገባ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ገለጹ።

በኢትዮጵያ የተጀመሩ ታላላቅና ዘመን ተሻጋሪ ችግር አስወጋጅ ሥራዎች እውን ማድረግ የሚቻለው ህዝቡ በአንድነትና በሕብረት ሲነሳ እንደሆነ ከህዳሴ ግድብ ተምረናል ነው ያሉት፡፡


 

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን በአደባባይ የሚከበረው የመስቀል ደመራ በዓል በመስቀል አደባባይ በደማቅ ሥነ-ሥርዓት እየተከበረ ነው፡፡

በክብረ በዓሉ ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ ብጹዓን አባቶች፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ወይዘሮ አበባ እምቢአለ፣ ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች፣ የተለያዩ ሀገሮች አምባሳደሮችና ጎብኚዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በክብረ በዓሉ ላይ ባስተላለፉት አባታዊ መልዕክት፤ እግዚአብሔር ጥፋትን የማይወድ አምላክ ነውና ሰዎች ከጥፋት ሊቆጠቡ ይገባል ብለዋል፡፡


 

የዘንድሮው የመስቀል ደመራ በዓል እግዚአብሔር የሰጠንን ውኃ በመጠቀም በአንድነት ተረባርበን የሕዳሴ ግድባችንን አጠናቀን ባስመረቅንበት ማግስት መሆኑ በዓሉን ልዩ ያደርገዋልም ነው ያሉት፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለሀገራችን ዳግም ልደትን ያበሰረ ስኬት መሆኑን በማንሳት፤ ለዚህ ላበቃን እግዚአብሔር እና በስራው ታሪካዊ አሻራቸውን ላስቀመጡ ሁሉ ምስጋና እናቀርባለን ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በቀጣይ ለመስራት በዕቅድ የያዘቻቸው ታላላቅ የልማት ስራዎችን በጥራትና በፍጥነት ተሰርተው ለህዝባችን ጥቅም እንዲውሉ መረባረብ እንደሚገባም አባታዊ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በኢትዮጵያ የተጀመሩ ታላላቅና ዘመን ተሻጋሪ ችግር አስወጋጅ ሥራዎች እውን ማድረግ የሚቻለው ህዝቡ በአንድነትና በሕብረት ሲነሳ እንደሆነ ከህዳሴ ግድብ ተምረናል ሲሉም ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም ህዝቡ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ያሳየውን ትብብርና ተነሳሽነት አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የመንበረ ፓትርያክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ብጹዕ አቡነ ሳዊሮስ በበኩላቸው መስቀል የሰው ልጆች ከፈጣሪ ጋር የታረቁበት ሰላም፣ ፍቅርና አንድነት የተገኘበት እርቅ የታወጀበት በዓል ነው ብለዋል።

መንፈሳዊ አንድነትን በማጠናከር ሀገርን ማገልገል ይገባል ሲሉም ነው የተናገሩት።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም