የዘንድሮ መስቀል ኢትዮጵያ አስቸጋሪና ፈታኙን ወቅት አልፋ የከፍታና የማንሰራራት ጉዞ በጀመረችበት ወቅት የሚከበር ልዩ በዓል ነው - ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ - ኢዜአ አማርኛ
የዘንድሮ መስቀል ኢትዮጵያ አስቸጋሪና ፈታኙን ወቅት አልፋ የከፍታና የማንሰራራት ጉዞ በጀመረችበት ወቅት የሚከበር ልዩ በዓል ነው - ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 16/2018(ኢዜአ)፦ የዘንድሮ መስቀል ኢትዮጵያ አስቸጋሪና ፈታኙን ወቅት አልፋ የከፍታና ማንሰራራት ጉዞ በጀመረችበት ወቅት የሚከበር ልዩ በዓል መሆኑን የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ ገለፁ።
የመስቀል ደመራ በዓል አከባበር የኢትዮጵያ ብዝሃ ባህል፣ ቋንቋ፣ ታሪክና እሴትን የሚያንፀባርቅ መሆኑንም ሚኒስትሯ ገልፀዋል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን በአደባባይ በድምቀት የሚከበረው የመስቀል ደመራ በዓል በመስቀል አደባባይ በደማቅ ሥነ-ሥርዓት እየተከበረ ነው፡፡
በክብረ በዓሉ ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ ብጹዓን አባቶች፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ወይዘሮ አበባ እምቢአለ፣ ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች፣ የተለያዩ ሀገሮች አምባሳደሮችና ጎብኚዎች ተገኝተዋል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ በዚሁ ወቅት እንዳሉት የመስቀል ደመራ በዓል አከባበር የኢትዮጵያ ብዝሃ ባህል፣ ቋንቋ፣ ታሪክና እሴትን የሚያንፀባርቅ ነው።
ከእነዚህ ፀጋዎች አንዱ የመስቀል በዓል መሆኑን ገልጸው፤ መስቀል ኢትዮጵያ በዓለም የምትታወቅበትና በዩኔስኮ በማይዳሰስ ቅርስነት የተመዘገበ የዓለም ሀብት መሆኑንም ተናግረዋል።
ይህም የጋራ የሚያደርገን የጋራ እሴት መኖሩን የሚያሳይ መሆኑንና ኢትዮጵያ በዘመናት የዳበረና በትውልድ ቅብብሎሽ የጎለበተ እምቅ የባህል ሀብት ያላት፣ ውብና ታሪካዊ ምድር ነች ብለዋል።
በመንፈሳዊና በመደበኛ አስተምህሮ የሰላምና ፍቅር መሰረት የሆኑ ትርክቶችን ለትውልድ እንዲደርሱ በትኩረት መስራት ይገባል ነው ያሉት።
ንግስት እሌኒ መስቀሉን ለማግኘት እጅግ ከባድ ፈተና፣ ድካምና ልፋት አልፋ በብዙዎች ትብብርና አንድነት ጥረቷ መሳካቱን ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያን እድገትና ብልፅግና ለማረጋገጥ የብዙዎችን ጥረትና ድካም ይጠይቃል ያሉት ሚኒስትሯ፤ ከልፋት በኋላ ውጤት እንደሚገኝ ትናንት የተጓዝንባቸው መንገዶች ያሳዩናል ብለዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በተባበረ ክንድ እንዳሳካነው በርካታ የምናሳካቸው የጋራ ድሎች ከፊታችን አሉ ይህንን ለማድረግ በህብረትና በአንድነት ቆርጠን ተነስተናል ነው ያሉት።
የዘንድሮ መስቀል ኢትዮጵያ አስቸጋሪና ፈታኙን ወቅት አልፋ የከፍታና ማንሰራራት ጉዞ በጀመረችበት ወቅት የሚከበር ልዩ በዓል መሆኑንም ተናግረዋል።
የተጀመረውን ጉዞ ከዳር ለማድረስ እንደ ደመራ ችቦ ተሳስረን በጋራ መነሳት የሚገባን ትክክለኛ ወቅት ላይ እንገኛለንም ነው ያሉት።