ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ እንደ መስቀሉ ፍለጋ መጽናት እንደ ደመራው መደመር ይገባናል-ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 16/2018(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ እንደ መስቀሉ ፍለጋ መጽናት እንደ ደመራው መደመር ይገባናል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን በአደባባይ በድምቀት የሚከበረው የመስቀል ደመራ በዓል በመስቀል አደባባይ በደማቅ ሥነ-ሥርዓት እየተከበረ ነው፡፡


 

በክብረ በዓሉ ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ ብጹዓን አባቶች፣ የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ወይዘሮ አበባ እምቢአለ፣ ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች፣ የተለያዩ አገሮች አምባሳደሮችና ጎብኝዎች ተገኝተዋል።

የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ መስቀል የኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅሩ የተገለጠበት፤ የሀይልና የጽናት ምልክት ነው፡፡

የመስቀል ደመራ በዓል በሚከበርበት ወቅት የመስቀሉን እውነታ ያሳያል፤ ወደ ብርሃን የምንሸጋገርበት ዘመን መሆኑንም ያበስራል ብለዋል፡፡


 

የዘንድሮው የመስቀል በዓል የሚከበረው የኢትዮጵያን የዘመናት ጨለማ የሚገፈው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በተጠናቀቀበት ወቅት መሆኑን በማነሳት፤ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያን እንደ መስቀል ደመራ ተደምረው በአንድነት መንፈስ ለፍጻሜ ማብቃታቸውን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያውያን ታሪካዊ ድል የሆነው የታላቁ ህዳሴ ግድብ በጸሎትና በፈጣሪ እርዳታ የመጣ በመሆኑም ለፈጣሪ ምስጋና ይገባዋል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን ከድህነት በመላቀቅ ብልጽግናን ለማረጋገጥ እንደ መስቀሉ ፍለጋ መጽናት እንደ ደመራው መደመር ይገባናል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ትጉሃን መስቀሉን የደበቀውን ቆሻሻ ንደው እንዳወጡት ሁሉ ኢትዮጵያውያን ተሰባስበን በመደመር ምሳሌ ተደምረን የኢትዮጵያን ጉስቁልና እየናድን ብልጽግናንዋን ማረጋገጥ ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡ 


 

የመስቀል ደመራ በዓል በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት የተመዘገበ መሆኑን በማስታወስ፤ በዓሉ ሀይማኖታዊ ትውፊቱን ጠብቆ እንዲከበር እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መዲናዋን እንደ ስሟ አዲስ፣ ለጎብኝዎች ሳቢ፣ ለአደባባይ በዓላት የተመቸች እንድትሆን ጥረት እያደረገ መሆኑን በማንሳት፤ በመስቀል አደባባይ የተገለጠው ውበት አንዱ ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም