የመስቀል ደመራ በዓል በመስቀል አደባባይ ኃይማኖታዊ ትውፊትና ሥርዓቱን ጠብቆ በድምቀት መከበር ጀምሯል - ኢዜአ አማርኛ
የመስቀል ደመራ በዓል በመስቀል አደባባይ ኃይማኖታዊ ትውፊትና ሥርዓቱን ጠብቆ በድምቀት መከበር ጀምሯል

አዲስ አበባ፤ መስከረም 16/2018(ኢዜአ)፦የመስቀል ደመራ በዓል በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ኃይማኖታዊ ትውፊትና ሥርዓቱን ጠብቆ በድምቀት በመከበር ላይ ይገኛል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን በአደባባይ በድምቀት ከሚከበሩት በዓላት መካከል የመስቀል ደመራ በዓል በየዓመቱ መስከረም 16 ቀን በመስቀል አደባባይ በደማቅ ሥነ-ሥርዓት ይከበራል።
በዘንድሮው ክብረ በዓል ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ ብጹዓን አባቶች እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን እምነት ተከታዮች ታድመዋል።
የአዲስ አበባ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ፣ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ወይዘሮ አበባ እምቢአለ፣ ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች፣ የልዩ ልዩ አገሮች አምባሳደሮች፣ ጎብኝዎች ተገኝተዋል።
በሥነ-ስርዓቱም በአዲስ አበባ የሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያንና አድባራት የሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራንና ሊቃውንት ኃይማኖታዊ ኅብረ ዝማሬን በማቅረብ በድምቀት እየተከበረ ይገኛል።
የመስቀል ደመራ በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት ተከታዮች ዘንድ ኃይማኖታዊ እሴትና ሥርዓታቸውን ጠብቀው በአደባባይ በድምቀት ከሚከበሩ በዓላት መካከል አንዱ ነው።
ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፤ የሳይንስና የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) የሰው ልጅ ወካይ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶችን ማስመዝገቧ ይታወቃል።
በአዘርባጃን ባኩ ከ23 እስከ 28 ቀን 2006 ዓ.ም በተካሄደው የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት የሳይንስና የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) 8ኛው ጉባኤ ወቅት የመስቀል ደመራ በዓል አከባበር ሥርዓትን የማይዳሰስ የዓለም ቅርስ አድርጎ መመዝገቡ ይታወሳል።
ኢትዮጵያ በዩኔስኮ የማይዳሰሱ ቅርሶች እስከአሁን ካዝመዘገበቻቸው መካከል የመስቀል ደመራ በዓል አከባበር ሥርዓት፣ ጥምቀት በዓል፣ ፊቼ ጫምባላላ፣ የገዳ ሥርዓት፣ ሸዋል ዒድና ሄራ ሂሳ ይገኙበታል።
በሚዳሰስ ቅርስነት የተመዘገቡት ደግሞ የሰሜን ተራሮች፣ አክሱም ሐውልቶች፣ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፣ የፋሲለደስ አብያተ መንግስታት ግንብ፣ የታችኛው ኦሞ ሸለቆ፣ ጢያ ትክል ደንጋዮች፣ የታችኛው አዋሽ ሸለቆ፣ ሐረር ጁገል፣ የኮንሶ ባሕላዊ መልክአ ምድር፣ መልካ ቁንጥሬ ባልጩት አርኪዮሎጂና ፓሎአትሮፖሎጂ፣ የጌዴኦ ባህላዊ መልዕክዓ ምድር፣ ባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ናቸው።